ሚያዝያ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 9/2007 ዓ.ም መስቀል አደባባይ ላይ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ቢያቅድም ፣ ማካሄድ እንደማይችል ተነግሮታል። አስተዳደሩ ‹‹መስቀል አደባባይ ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ ያለበት
ከመሆኑም በላይ በርካታ የተከማዋ ነዋሪ የሚተላለፍበት እና የከተማው ነዋሪ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር ነው” በማለት ጥያቄውን አለመቀበሉን ገልጿል።
መንግስት በቅርቡ በደቡብ አፍሪካና በአይ ኤ ኤስ የተገደሉትን ኢትዮጵያውያንን ለመቃወም በመስቀል አደባባይ ሰልፍ እንዲደረግ መፍቀዱ ይታወቃል። ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ ተቃዋሚዎች በግንባታ ወይም በትራፊክ ፍሰት ሰበብ በመስቀል አደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ
እንዳያደርጉ መከልከላቸው ይታወቃል። በሌላ በኩል ደግሞ በአዲስ አበባ በ10ሩም ክ/ከተማዎች በጥቆማ የሚታሰሩ ወጣቶች ቁጥር ጨምሯል።
ብዙዎች የሰማየዊ ፓርቲ አባል ነህ ወይ እየተባሉ እየተጠየቁ የሚታሰሩ ሲሆን፣ በ1ለ5 አደረጃጀትና የሴቶች ልማት ቡድን ተብለው በተሰባሰቡ ሴቶች አማካኝነት ለጠቋሚዎች 50 ብር እየተሰጠ ወጣቶች በገፍ እንዲታሰሩ እየተደረገ ነው።
የታሰሩ ወጣቶች ደግሞ ማታ ማታ ላይ ለየብቻ እየተጠሩ በደህንነቶች ኩላሊታቸውን በጎማ ዱላና በቦክስ እየተደበደቡ በከፍተኛ ህመም ላይ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ደህንነቶች የጠረጠሩትን ወጣት እየያዙ በደንብ ከፈተሹ በኋላ ሞባይል ስልክ ቀምተው ሀገራዊ ዘፈኖችና የታረዱ ወገኖችን ፎቶ የያዙ ሰዎችን አንተ ሰማያዊ ነህ ብለው አፍሰው ያስራሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ሰማያዊ ፓርቲን በግልጽ በተከታታይ በመገናኛ ብዙሃን በአሸባሪነት በመፈረጅና በማስፈራራት ሥራ መጠመዱ በፓርቲው ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሁኔታዎችን እያመቻቸ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ።