በኢትዮጵያ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች በዲዛይንና ችግርና በሙስና ታክስ ከፋዩን ህዝብ ከፍተኛ ወጪ እያስወጡት ነው

ሚያዝያ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ብቻ በዲዛይንና በሙስና በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በመባከኑ፣ ግብር ከፋዩ ለአላስፈላጊ ወጪ ይዳረጋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለቤትነት በፌደራል የውሃ ዲዛይንና ቁጥጥር ድርጅት አማካሪነት እና በፌደራል ውሃ ስራዎች ቁጥጥር ድርጅት ተቋራጭነት የግንባታ ስራው እየተካሄደው ባለው የርብ መስኖና ግድብ ፕሮጀክት ጥልቅ የዳሰሳና አዋጭነት ጥናት ባለመሰራቱ የዲዛይን ለውጡ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አስወጥቷል። በቆጋ መስኖ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት በ405 ሚሊዮን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ስራው ሲጠናቀቅ 715 ሚሊዮን ብር በማስወጣቱ፣ ገብር ከፋዩ 310 ሚሊዮን ብር ከ42 ሳንቲም ተጨማሪ እንዲከፍል ተገዷል።

እንደሰነዱ በየርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት፣ በቆጋ መስኖና ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት፣በቆቦ ጊራና የከርስ ምድር መስኖ ፕሮጀክት፣በጊዳቦ እና በዝዋይ መስኖ ፕሮጀክቶች የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት ቢደረግም፣የተሰጡ አስተያየቶችን ተግባራዊ ለማድረግና ለማስፈጸም የጥናት ሰነዱ(ዶክመንቱ) በአማካሪዎችና ተቋራጮች እንዲሁም በአስፈጻሚ አካላቶች እጅ አልገባም።

በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ከውጭ ሀገር ተበድሮ በመልሶ ማበደር ስምምነት ለልማት ድርጅቶች ያበደረውን ገንዘብ ተበዳሪዎች በገቡት ውል መሠረት ወቅቱን ጠብቀው ተመላሽ ማድረግ ባለመቻላቸው ከ 9 መስሪያ ቤቶች በድምሩ 100 ሚሊዮን ፣ 920 ሺ 131 ብር ከ52 ሳንቲም ላለፉት አራት አመታት መመለስ  አልቻሉም።   ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተበድረው መመለስ ካልቻሉት ድርጅቶች ውስጥ የኢት- ጅቡቲ ምድር ባቡር ፤ ወንጅ ስኳር ፋበሪካ ፤ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ  እንዲሁም ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ይገኙባቸዋል።