ሚያዝያ ፭(አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ታስረው ከሚገኙት ፖለቲከኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች መካከል ወጣት ብርሃኑ ተክለያሬድና ፍቅረማርያም አስማማው የረሃብ አድማ ጀምረዋል። የረሃብ አድማው መንስኤ ወጣት
እየሩሳሌም ተስፋው በቤተሰቦቿ የመጎብኘት ፈቃድ በመከልከሏ፣ በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ለብቻዋ ታስራ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባት በመሆኑ፣ ድርጊቱን ለመቃወም ነው።
ወጣት ብርሃኑና ፍቅረማርያም በምርመራ ወቅት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ምንጮች ገልጸዋል። በአሁኑ ጊዜ ቃላቸውን ሰጥተው ድብደባው የቆመላቸው ቢሆንም፣ በእየሩሳሌም ላይ የሚደርሰው ስቃይ ግን እንደጨመረ ነው።
በእየሩሳሌም ላይ የሚደርሰው ስቃይ እስካላበቃና ቤተሰቦቿ እንዲያዩዋት እስካልተፈቀደ ድረስ በረሀብ አድማው እንደሚገፉት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ገልጸዋል።
ብርሃኑ ተክለያሬድ ፣ እየሩሳሌም ተስፋውና ፍቅረማርያም አስማማው ከዚህ ቀደም በተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በመሳተፋቸው ታስረው ተደብድበዋል።
ወጣቶቹ በምን ምክንያት እንደታሰሩ እስካሁን በይፋ መግለጫ የሰጠ አካል የለም። ይሁን እንጅ በቅርቡ ፍርድ ቤት በቀረበቡበት ወቅት፣ ሶስቱም ወጣቶች ከግንቦት7 ጋር በተያያዘ መከሰሳቸው ተገልጿል።