የጋምቤላ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ጥምረት ንቅናቄ የኢትዮጵያ መንግስት ለደቡብ ሱዳን አማጽያን የሚሰጠውን ድጋፍ ተቃወመ

ሚያዝያ ፭(አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጥምረቱ ለኢሳት በላከው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት የሳልቫኪርን መንግስት ለሚቃወሙት ለደቡብ ሱዳን አማጽያን ድጋፍ እየሰጠ፣ በሌላ በኩል የሰላም ስምምነት አደራዳሪ ሆኖ መቅረቡ ትክክል አይደለም ብሎአል።

የአዲስ አበባው መንግስት የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሃይሎችን ለመሸምገል ገለልተኛ አይደለም የሚለው መግለጫው፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለተቃዋሚዎች ወታደራዊ ስልጠና፣ የሎጅስቲክስና ወታደራዊ ድጋፍ እያደረገላቸው ነው ብሎአል።

ድርጊቱ የአካባቢውን ሰላም የሚያናጋና አለመረጋጋትን የሚፈጥር ነው ሲል ጥምረቱ አስጠንቅቋል።

በኢትዮጵያ መንግስት የሚደገፉት አማጽያን በጋምቤላ ክልል ድንበር አካባቢዎች እንደፈለጋቸው እየተንቀሳቀሱ ነው የሚለው መግለጫው፣ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ዝውውር መኖሩ አካባቢውን ወደ ትርምስ ሊከተው እንደሚችል ገልጿል።

ከደቡብ ሱዳን የሚፈልሱትን ስደተኞች የአዲስ አበባ መንግስት ተወላጆች በሚኖርቡት አካባቢ በብዛት ማስፈሩ ችግር እየፈጠረ መሆኑን፣ ስደተኞች በክልሉ ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባት መጀመራቸውን በማስታወስ ፣ ሁኔታው በጊዜ ካልተገታ በአካባቢው አለመረጋጋት እንደሚፈጠር ንቅናቄው አስጠንቅቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት አድልኦ የተሞላበት የሽምግልና ጥረት በጽኑ ሊወገዝ እንደሚገባ ቢገልጽም፣ ሁለቱም ሃይሎች በአካባቢው ለሚፈጠረው ሰላም  ሲባል የሰላም ስምምነቱን ተቀብለው ተግባራዊ እንዲያድረጉ ጠይቋል።

የማቻር ድርጅት የደቡብ ሱዳን መንግስት የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች ይረዳል የሚል ወቀሳ ማሰማቱ ይታወቃል።