መጋቢት ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በባህር ዳር ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተማዎችና ሙሉዓለም አዳራሽ የተደረገው ስብሰባ የተፈለገውን ግብ ሳይመታ መጠናቀቁን የስብሰባው ተሳታፊዎች ተናገሩ፡፡
ቅዳሜ መጋቢት 26/2007 ዓ.ም በተደረገው ስብሰባ የብአዴን አባላትን በጥሪ ወረቀት የከተማ ነዋሪዎችን ቤት ለቤት በመዞር በስብሰባው እንዲገኙ በመመዝገብና የተለመደውን ማስፈራሪያ በመጠቀም እስከ ቀኑ 6 ሰዓት በተደረገው ስብሰባ ተሳታፊዎች የተለያዩ
ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን በመስጠት የገዢውን መንግስት ካድሬዎች ሲያሸማቅቁ መዋላቸውን ተሳታፊዎች ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
ያለፈውን አምስት ዓመት “ የህዝቡ ችግር ምንድን ነው? ” በማለት ሰብስባችሁ ሳታነጋግሩን ዛሬ የምርጫ ወቅት ሲደርስ በመሰብሰብ መልካም ሰርተናል ለምን ትላላችሁ?
ከምርጫ ቀን በኋላ የምትገቡትን ቃል ሁሉ በመርሳት ከጥቃቅን አገልግሎቶች ጀምሮ ህዝቡን በመልካም አስተዳደር እጦት ማሰቃየት እንደ ልማድ አድርጋችሁ የምትሰሩበት አካሄድ ሆኖ እያለ፤ ዛሬ ለምርጫ ሲባል ራሳችሁን እንደ ቅዱስ አድርጋችሁ ለምን ታቀርባላችሁ?
የገዢው መንግስት ስራውን በአግባቡ አለመስራቱን በተለያየ የአፈጻጸም ስራዎች ታይቷል፡፡ ህዝቡ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ባለበት ወቅት በዘይትና ስኳር ሰበብ ህዝቡን ከአንድ አመት በላይ ለሌላ ሰቆቃ ዳርጋችኋል፡፡ይህም አመራራችሁ ከዘመኑ ፍጥነት ጋር ለመጓዝ
እንዳልቻለ ያስረዳልና አመራሩን ከታች ጀምሮ በተማሩ ሰዎች እንዲያዝ ለምን አታደርጉም?
ከክፍለ ከተማው ዝቅተኛ ሰራተኛ ጀምሮ እስከ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሙያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በሙስና እየተዘፈቁ የራሳቸውን ሃብት ሲያከማቹና በህዝቡ ላይ ልዩ ልዩ ተጽእኖ ሲያደርሱ ይህን በመከላከል ህብረተሰቡን ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኝ
ከማድረግ ይልቅ ዝምታን የመረጣችሁበት ጊዜ ነው፡፡ዛሬ ሙስና እንደ ህጋዊ አሰራር ተቆጥሮ ማንኛውም አሰራር ያለ እጅ መንሻ የማይፈጸምበት ጊዜ ላይ ቆማችሁ መልካም ሰራን ማለቱ ዋጋ ያሰጠዋል ወይ?
አገራችን አደገች ስትሉ በየጊዜው እንሰማለን፡፡የጥራታቸውን ጉዳይ ሳናነሳ በመንግስትና ህብረተሰቡ መዋጮ የተሰሩ የኮብልስቶን መንገዶች አሉ፡፡ሀገር አቋራጭ መንገዶችም ደረጃቸው አድጎ ተመልክተናል፡፡ በሌላ መልኩ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች ምንጩ
ባልታወቀ ሁኔታ ከመሬት ተነስተው ህንጻ ሲገነቡ እናያለን፡፡በእያንዳንዱ ቤተሰብ ኑሮ ላይ የሚታይ ለውጥ ሳይኖር አድገናል የሚለው መግለጫ ምን ማለት ነው?እድገት ሁሉን ያማከለ ነው ትላላችሁ ታዲያ እድገቱ የታለ? እኛ ሲያድጉ፣መኪና ሲቀያይሩ፣
ቤተሰባቸውን ሲያቀማጥሉና በየቦታው ህንጻ ሲገነቡ የምናያቸው በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦችን ብቻ ነው፡፡ሁሉን ያማከለ ዕድገት ሳይኖር አድገናል ማለቱ ህዝቡን ማታለል አይሆንባችሁም?
በከተማም ሆነ በገጠር ያለው መሬት በተወሰኑ ግለሰቦች፣ አመራሮችና ቤተሰቦቻቸው ከመያዙ ባሻገር ከዓመት ዓመት እየባሰ መሄዱ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት ሆኗል፡፡ወጣቶች መሬት በማጣት ወደ ከተማ መፍለሳቸውና ወደ አረብ ሃገራት
መሰደዳቸው ችግር ሆኖ ቢቀጥልም የተሰጠ መፍትሄ የለም፡፡መሬት በጥቂት ሃብታሞችና ለመንግስት ታማኝ በሆኑ ግለሰቦች እጅ መሆኑ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በቤት ክራይ እንዲሰቃይ አድርጎት ይታያል፡፡ታዲያ ፍትሃዊነትን አስፍነናል ለማለት
የሚያስደፍር ስራ አላችሁ ወይ? የሚሉና የመሳሰሉ በገዢው መንግስት የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በድፍረት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
የገዢው መንግሰት ካድሬዎች በቅስቀሳው መልካም ውጤት እንገኛለን በማለት ከተለያየ መስሪያ ቤቶች የሰበሰቧቸው የመንግሰት ሰራተኞችን በሙሉዓለም አዳራሽ ፤ በክፍለ ከተሞች ለተሰበሰበው ህዝብ ለስላሳ፣ቆሎ፣ውሃናዳቦ በማቅረብ ቡና በማፍላት የ24
ዓመቱን የኢህአዴግ ጉዞ ያስገኘውን ለውጥ በማጋነን ቢያወሩም በታሰበው መልኩ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ የሚቀይር ውጤት እንዳልተገኘ በስፍራው የታደሙ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
የዚህ ዜና ሙሉ ዘገባ በሚቀጥሉት ቀናት ይቀርባል።