መጋቢት ፲፯(አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በመቶ ሚሊየን በሚገመት ወጪ በታላቅ ፌሽታ እያከበረ የሚገኘው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አመራር በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች
ትምህርት ቤቶችን እስከማዘጋት የደረሰውን የመጠጥ ውሃ ችግር ሊታደግ ያልቻለ መሆኑን መረጃዎች ጠቆሙ፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር የወጣ አዲስ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው የመጠጥ ውሃ ችግር ሕዝብን ለከፍተኛ ችግር ከመዳረጉም አልፎ የመማር ማስተማር ስራ በማደናቀፍ ትምህርት ቤቶችን እስከማዘጋት ደርሷል።
የመጠጥ ውሃ ችግር ከገጠማቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች መካከል በአርሲ ዞን በጎሎልቻ፣ መርቲ፣ .ዝዋይ፣ ዱግዳ፣ ሴሩና ደጁ ወረዳዎች፣ በምዕራብ አርሲ ዞን በሻላ ሲራሮና ሻሸመኔ ወረዳዎች፣ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በሚደጋ፣ ቁምቢያ መዩ ወረዳዎች፣ በምስራቅ
ሸዋ ዞን በቦሰት ወረዳ እና በጉጂ ዞን በሊበንና ሰባቦሩ ወረዳዎች አስከፊ የተባለ የመጠጥ ውሃ ችግር ማጋጠሙን ሚኒስቴሩ አጋልጦአል፡፡
የመጠጥ ውሃ ችግሩ በተለይ በአርሲ ዞን በዝዋይ ዱግዳና በሴሩ ወረዳዎች፣ በጉጂ ዞን በሊበን ወረዳ ት/ቤቶችን እስከማዘጋት የደረሰ ችግር መከሰቱ ተረጋግጦአል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የተከሰተውን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ ከአጋር ድርጅቶች
ባገኘው ድጋፍ ውሃ በቦቴ የማደል ስራ እያከናወነ መሆኑ ታውቋል፡፡
በቦረና ዞን አንዳንድ ወረዳዎች ማለትም በአሬሮ፣ ድሬ፣ ዲሎ፣ ዳስ የእንስሳት መዳከምና ሞት መከሰት የጀመረ ሲሆን በአርሲና ምዕ/ሐረርጌ ዞኖች የእንስሳቱ አቋም እየተዳከመ መሆኑ፣ የእንስሳት እንቅስቃሴም ተጀምሮ በምዕ/ሐረርጌ ዞን ከቡርቃ ዲምቱና ሃዊ
ጉዲና ወደ ዱንገታና ዋቤ ወንዝ፣ በቦረና ዞን ከተልተሌ ወደ ገራንና ኮንሶ፤ ከድሬ፤ ሚዮና ሞያሌ ወደ ኬንያ (አዋሳኝ ቦታዎች) በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል።
የኦሮሚያ ክልል ገዥ ፓርቲ ኦህዴድ/ኢህአዴግ እንዲህ ዓይነቱን የህዝብ ችግር ሳይፈታ ለክብረበአል በመቶ ሚሊየን ብሮችን ሲያፈስ መታየቱ አሳዛኝ መሆኑን ዘጋቢያችን ያነጋገርናቸው የኦሮሞ ተወላጆች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአማራ ክልል ደግሞ በሰ/ሸዋ ዞን በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ፣ በሰ/ጎንደር ዞን በምስራቅ በለሳ ወረዳ በእያንዳንዳቸው 3 ቀበሌዎች የውሃ እጥረት፣ በዋግኸምራ ዞን በሳህላ፣ ዝቋላና ሰቆጣ ወረዳዎች፣ በሰ/ወሎ ዞን በላስታና ቡግና ወረዳዎች፣ በደ/ወሎ ዞን በመቅደላ
ወረዳ በ4 ቀበሌዎች፣ በኦሮሚያ ዞን በአ/ፉርሲ ወረዳና በምስ/ጎጃም ዞን ቆላማ አካባቢዎች የውሃ እጥረት ተከስቷል።
በሀረሪ ክልል በ5 ቀበሌዎችና በድሬዳዋ አስተዳደር ቆላማ ቀበሌዎችም ተመሳሳይ ችግር ተከስቷል። ችግሮችን ለመቅረፍ ውሃ በቦቴ ለማደል ሙከራ መደረጉም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።