መጋቢት ፲፬(አስራ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለኢህአዴግ መንግስት ቅርበት ያላቸው የመገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ አየር ሃይል ኤርትራ ውስጥ የሚገኘውን ቢሻ የማእድን ማውጫ ኩባንያን መደብደቡን ቢዘግቡም፣ በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል
በይፋ የተሰጠ ማረጋጋጫም ሆነ ማስተባበያ አልተገኘም። ይሁን እንጅ የኩባንያው 60 በመቶ የአክሲዮን ባለቤት የሆነው ተቀማጭነቱ ካናዳ የሆነው ኩባንያ ፣ በማእድን ማውጫው ላይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መጠነኛ ጥፋት ወይም በእንግሊዝኛ ቫንዳሊዝም መፈጸሙን
በማተት ፣ የተበላሹት ማሽነሪዎች ተጠግነው ወደ ስራ እንደሚገባ አስታውቋል። ኩባንያው ጥፋቱን ማን እንዳደረሰው ባያብራራም፣ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ግን ገልጿል።
ፋብሪካው ከ10 ቀናት በፊት በአንደኛው የስራ ክፍል ብልሽት አጋጥሞት የነበረ ቢሆንም ፣ ችግሩን በማስተካከል በዚህ ሳምንት ወደ ስራ ለመግባት መታቀዱን ኩባንያው ጠቅሷል። ይሁን እንጅ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በማሽኖች ላይ መጠነኛ ጉዳት ቢደርስም በአጠቃላይ
ስራው ላይ ተጽኖ አለማምጣቱንና በሰው ህይወት ላይም ያደረሰው ጉዳት እንደሌለ ገልጿል።
ጥፋቱ በፈረንጆች ኦቆጣጠር ማርች 20 ሌሊት ላይ መፈጸሙን የጠቀሰው ኩባንያው፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን መጠነኛ ብልሽት በዚህ በመጠገን ፋብሪካው በሳምንቱ አጋማሽ ወደ ስራ ይገባል ብሎአል።
ኒቭሱን ኩባንያ በኤርትራ የሚያካሂደው የማእድን ማውጣት ስራ ትርፋማ መሆኑንም በመግለጫ ጠቅሷል።
ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ያላቸው የመገናኛ ብዙሃን ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ወድሟል ሲሉ ዘግበው ነበር። ኩባንያው ግን የደረሰውን ጥፋት አቃሎ በማየት ዜናውን አጣጥሎታል።