2ኛው ሀገር አቀፍ የተማሪዎች ሰፖርታዊ ውድድር በመጋቢት ወር መካሄዱ በትምህርት ጊዜቸው ላይ ተጽእኖ እንዳሳደረባቸው ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

መጋቢት ፲፭(አስራ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ በመካሄድ ላይ ባለው 2ኛው የትምህርት ቤቶች ውድድር ተገኙት ተወዳዳሪዎች እንደተናገሩት በውድድሩ በርካታ አዳዲስ ተተኪ ወጣቶች ለማፍራት የሚያስችል  ቢሆንም ወቅቱን

የጠበቀ አለመሆኑ በትምህርታቸው  ላይ ጉዳት እንደሚያደርስባቸው ተናግረዋል፡፡

ከመጀመሪያው መንፈቅ አመት ፈተና በኋላ በቀጥታ ወደ ስፖርት ውድድር ልምምድ በመግባታቸው፣  ከትምህር ገበታቸው ላይ ለሁለት ወር ያህል መለየታቸውንና ከዛም  ለውድድር ወደ ባህርዳር መምጣታቸውን የሚናገረው ተወዳዳሪ ተማሪ ነስረዲን፣  ከሌሎች

ተማሪዎች ጋር በመሆን ትምህርት ለመቀጠል አለመቻላቸው በውጤታቸው  ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርባቸው  ተናግሯል፡፡

“ከውድድር በኋላ ያለንን ትርፍ ሰዓት ለጥናት የምንጠቀም ቢሆንም ከተማሪዎች ጋር በክፍል በመገኘት አብረን አለመከታተላችን ከመምህራን የሚገኘው ትምህርት ያመልጠናል፡፡”በማለት የውድድሩ ጊዜ ትምህርት በሌለበት የክረምት ወቅት በማድረግ  ጊዜውን

ማስተካከል ይገባ  እንደነበር አክሏል።

በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ ለውድድር የመጣችው ተማሪ ቆንጅት ” የ10ኛ ክፍል ተማሪ በመሆኗ ለፈተና መዘጋጀቱ ቀርቶ እዚህ ለውድድር መገኘቷ ለአእምሮዋ እንደከበዳት” ትናገራለች፡፡ይህ ውድድር ቢቻል በክረምት ትምህርት ሲዘጋ ቢደረግ ጥሩ እንደሆነ የሁሉም

ተማሪዎች ሃሳብ ነው ብላለች።

የስፖርቱት ውድድሩ  ከመጋቢት 6 እስከ መጋቢት 20/2007 ዓም.በመካሄድ ላይ ሲሆን በሁሉም ክልሎች እና የከተማ እስተደዳሮች ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተወጣቱ ከ3 ሽህ በላይ ተሳታፊዎች አሉት፡፡

ውድድሩ በመጀመሪያው መንፈቅ አመት የትምህርት ቤቶች  ዝግ መደረግ እየቻለ በዚህ ጊዜ የተካሄደው ገዢው መንግስት የመከላከያ ሰራዊት በዓልን ለማክበር በሚል የባህርዳርን ብሄራዊ ስቲዲየምን እስከ የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም  በሚከበረው በስፖርታዊ

ውድድሮች፣ በኤግዚቢሽን፣ በፓናል ውይይትና በኪነጥበባት ውድድር  እና ልዩ ልዩ ዝግጅት በመያዙ ሲሆን፤ በትምህርት ሰአት ይህን ያህል ጊዜ ተማሪዎቹን ከትምህርት ገበታ ማለያየቱ አግባብ እንዳልሆነ ስማቸውና ድምጻቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የድል ችቦ ሙሉ

ሳይክል ትምህርት ቤት መምህራን ለዘጋቢያችን  ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ጥራት፣  ትምህርት ማቋረጥ እንዲሁም አዘውትሮ በትምህርት ገበታ ላይ አለመገኘት የትምህርት ስርአቱ ዋና  ችግሮች መሆናቸውን ክልሉ በቅርቡ ባደረገው ስብሰባው አስታውቋል።