ኢሳት ዜና:-ህጻን ሀያት መስከረም 12/2000 ዓ.ም በእቅፍ ነው ስደት የወጣችው። ገና የአንድ አመት ልጅ እያለች ነው በባህር ወደ የመን ከመጡት እናቷ እና አባቷ ጋር አብራ የመጣችው። ድንገት ማንም ሰው በዚህ እድሜው ከሚያየው ስቃይ በላይ ስቃይን አጣጥማለች። እናቷ በሞት የተለየቻት ይህች ህጻን እንዳዛሬው 5 ዓመት ሞልቷት መሳቅ መጫወት ሳትጀምር፣ ርሀብ ጥሟን መናገር ሳትችል፣ ህመሜ እዚህ ጋር ነው በማትልበት ወቅት የ 11 ወር ልጅ ሆና ነው ። አባቷ የወንድ ጡቱን እያጠባት፣ ውሀ ጥም ሲያስለቅሳት ምራቁን እየሰጣት፣ ጡቱ ጠብ የሚለው ሲጠፋ ምላሱን እያጠባት ያን በረሃ ይዟት አለፈ።
መንግስቱ ለገሰ ዛሬ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ስሙን ቀይሮ ካሊድ ተብሎ ነው የመን ስደተኛ የሆነው። ወደ የመን ሲመጡ የባህር ጉዞውን አጠናቀው ልክ የየመንን መሬት ሊረግጡ ሲሉ ነው እናቷ የሞተችው። በህገ-ወጥ መንገድ በባህር የሚያጓጉዙትን ሶማሊያዊያን ለመያዝ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ በጥይት ተመታ ባህሩ ዳር ህይወቷ ያለፈው ሚስቱን አንብቶ ቀበረ። ሀዘን ያቆራመደው ካሊድ ልጁን ማትረፍ ነበረበትና ጡቱን እያጠባ..ኤደን የሚባለው የየመን ሁለተኛ ከተማ ድረስ ለመድረስ በመሀል በመሀል ያሉት ትናንሽ ከተማዎች ውስጥ እየለመነ ውሀ፣ ወተት.. እያቀመሳት ሶስት ቀንና ሶስት ሌሊት ተጓዘ።
ኤደን የሚባለው ከተማ እንደገቡም UNHCR አልቀረስ በሚባለው የኦሮሞ ተወላጆች እና ሶማሊያዊያን የሚሰቃዩበት ካምፕ ግቡ ተባሉ።
ከባህር ሲወርዱ ጀምሮ በበሽታ የተለከፈችው ህጻን ለወራት ህክምናውን አገም ጠቀም በሆነ ሁኔታ ተከታተለች። አልዳነችም። ለጊዜው ቢሻላትም በሰዓቱ ወደ ውስጧ የገባው የባህር ውሃ ለተለያየ በሸታ ዳረጋት። በህመምም ለ4 ዓመታት ታግላ ተጓዘች። ዛሬ ግን ችላ መጓዝ አልቻለችም። በአሁኑ ሰዓት ሆስፒታል በሞትና ህይወት መካከል ያለች የ5 ዓመት ልጅ ነች።
አይኗ አያይም ጆሮዋ አይሰማም። በምግብ እጥረት ከሚመጣ በሽታ በተጨማሪ የአእምሮ ችግር በሚያስከትል በሽታ አልጋ ላይ ውላለች። ሰውነቷ በጣም ከመጎዳቱ በላይ ሆስፒታል በውስጥ ተኝታ ስትታይ ያለች አትመስልም። እንደ ዶክተሮቹ አባባል በጣም ከፍተኛ ህክምና ያስፈልጋታል:፡
የመን ያለ ሀበሻ በዚህ ሰዓት ሁሉም መለመን አፍሮ እንጂ ተቸግሯል። በመጀመሪያ ደረጃ የሚያሰፈልጋት የውጭ ሀገር ህክምና ነው። ይህን ማመቻቸት የምትችሉ በህክምናው መስክ የተሰማራችሁ፣ ግብረ ሰናይ ድርጅት ያላችሁ..ከግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ጋር ግንኙነት ያላችሁ በበርካታ በሽታ የታጠረች ልጅ ለማዳን እንዲረባረቡ ወላጅ አባቱዋና ጋዜጠኛው ተማጽነዋል።
ህጻን ሀያትን ለመርዳት ከፈለጋችሁ ለአባቷ በ 00967735241562 በመደወል ወይም በጋዜጠኛው ግሩም ተክለሀይማኖት በኩል በ 00967735126401 በመደውል ገንዘብ ለመላክ እንደምትችሉ ለመግለጥ እንወዳለን።