ኢሳት በሳተላይት የ24 ሰዓት ሬዲዮ ስርጭት ጀመረ (የኢሳት ጋዜጣዊ መግለጫ)

 
ኢት ሳተላየት ቴሌቪዥን (ኢሳት)

ጥቅምት 20 ቀን 2004 ዓም

ኢሳት የ24 ሰዓት የሳተላይት ራዲዮ ስርጭት ማስተላለፍ መጀመሩን በተመለከተ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፣

የኢትዮጵያ ሳተላየት ቴሌቪዥን (ኢሳት) የሰተላይት ራዲዮ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ማስተላለፍ መጀመሩን ለህዝብ ሲያሳውቅ በታላቅ ደስታ ነው።

ኢሳት የሳተላይት ራዲዮ ስርጭት የጀመረበት ዋና ምክንያት ለኢትዮጵያ ህዝብ ለዴሞክራሲና ለነጻነት ለሚያደርገው ትግል ህዝብ ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ትግሉን ለማገዝ የገባውን ቃል አጠናክሮ ለመቀጠል ነው። ከዚህም በተጨማሪ የመለስ አገዛዝ ኢሳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስርጭቱን ማስተላለፍ በጀመረበት የአጭር ሞገድ ራዲዮ ላይ የከፈተውን የአፈና ዘመቻ ለመቋቋም የስርጭት አድማሱን  ለማስፋት በማሰብ ነው። ይህም ሆኖ በአጭር ሞገድ ስርጭቱ ላይ የተከፈተውን የአፈና ዘመቻ ለመቋቋም ፕሮግራሙን የሚያስተላልፍበትን የሞገድ ጉልበት ከፍ አድርጓል።

የኢሳት የሳተላይት የራዲዮ ስርጭት አገልግሎት በቀን 24 ሰዓት የሚተላለፍ በመሆኑ አድማጮች በተመቻቸው ጊዜ ፕሮግራሞቹን መከታተል ይችላሉ።

የኢሳት የ24 ሰአት የሳተላይት ራዲዮ የሚተላለፍበት ዝርዝር መረጃ፣

  • AB 2 Satellite
  • KU Band
  • 8 Degrees West
  • Transponder = D-8
  • Downlink Frequency = 11595 Vertical
  • Symbol Rate = 27500
  • FEC = 3/4

መሆኑን እየገለጽን በሀገርም ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገሮች የምትገኙ ዜጎች ይህንን መረጃ በምትችሉት መንገድ ሁሉ በሀገርም ውስጥ ሆነ በውጭ ለሚገኙ ወገኖች በማስተላለፍ ለዴሞክራሲና ለነጻነት ለሚደረገው ትግል የበኩላችሁን ሀላፊነት እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

በመጨረሻም ኢሳት የኢትዮጵያ ህዝብ ለዴሞክራሲና ለነጻነት በሚያደርገው ትግል እንደ አንድ የመረጃ ምንጭ በመሆን የራሱን አስተዋጽዖ ለማድረግ የገባውን ቃል ኪዳን እንደገባ በማደስ የኢትዮጵያ ህዝብ የሀገሩና የመብቱ ባለቤት እስኪሆን ድረስ እንደ አንድ የትግል ግንባር በመሆን ትግሉን የመርዳት ጥረት በሚችለው ሁሉ እንደሚቀጥል እያስታወቀ፣ በዚህም ጥረቱ መላው ለዴሞክራሲና ለነጻነት የቆማችሁ ወገኖች በሙሉ በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጀመረውን እርዳታ የማሰባሰብ ዘመቻ ውስጥ በመሳተፍ የሚቻላችሁን ሁሉ እንድታደርጉ ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል።

የኢሳት የነጻነት መንፈስ ለዘላለም ይኑር!!!

የኢሳት የበላይ አስተዳደር፣

www.ethsat.com