ጥር ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ብአዴን ) ፤የድርጅቱን የትግል ጉዞ የሚተርክ አዲስ መፅሃፍ አስጽፎ የድርጅቱ መስራች በሆኑትና በቅጽል ስማቸው <<ጥንቅሹ>>ተብለው በሚጠሩት በአቶ ታደሰ ካሳ እያስገመገመ ሲሆን፤ በመጽሀፉ ይዘት ላይ በአመራሮቹ መካከል ላይ ከፍተኛ አለመግባባት ተፈጥሯል።
በግምገማው ላይ የብአዴን መስራች አይደለህም የተባሉት ታደሰ ካሳ፤ << ለላፉት 30 ዓመታት የማላውቀው ታሪክ ነው የተነገረኝ>> ሲሉ በንዴት ተናግረዋል።
አቶ ታደሰ ይህን ሲሉ በጓዶቻቸው ፦ መስራቾች ከ37 ታጋይነት ወደ36 ዝቅ እንዲሉ መወሰኑንና እርሳቸውም መስራች ባለመሆናቸው ስማቸው እንዲወጣ መደረጉን ሲነገራቸው ከፍተኛ ንዴት ውስጥ ከመግባታቸውም ባሻገር አመራሮቹ ለሁለት ተከፍለው እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ሲከራከሩና ሲጨቃጨቁ አምሽተዋል።
በውይይቱ፤ መጽሀፉ ታደሰ ካሳን ከመስራችነት በማውጣት እንዲታተም የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ በመነሳቱ አቶ ታደሰ ካሳ እንባ አውጥተው እስከማልቀስ መድረሳቸውን ምንጮቻችን ጠቁመዋል። በመጨረሻም አቶ ታደሰ ካሳ ወይም ጥንቅሹ የብአዴንን ጉዞ በሚተርከው በፅንአት ቁጥር አንድ እና ሁለት መፅሃፍ ስማቸውን በመስራችነት ጠቅሰው ቢጽፉም፤ የድርጅት ጓዶቻቸው በመስራችነት እውቅና እንደማይሰጧቸው በማስረገጥ ውይይታቸውን አጠናቀዋል።
በአሁኑ ስዓት በፖለቲካ ጫና ዳር እየወጡ ያሉት አቶ ታደሰ ካሳ፤ የብአዴን የልማት ድርጅት የሆነውን ጥረት ኮርፖሬትን እንዲመሩ ተመድበዋል። ብአዴን- ኢህአዴግ ከድሮው የኢትዩጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅንቄ (ኢህዴን) ተፀነሶ የህውሃትን ህልም ለማሟላት ሲል ከህብረ ብሄራዊነት ወደ ብሄር ድርጅትነት መቀየሩ ይታወቃል።