ጥር ፲፰(አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መጪውን ምርጫ ተከትሎ ራዲዮ ፋና “ሞጋች” በተሰኘ ፕሮግራሙ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ለውይይት በመጋበዝ በተለይም አመጽ ቀስቃሾች መሆናቸውን በሚያሳጣ መልኩ ፕሮግራሞችን ሲለቅ ቆይቷል።
ባለፈው ሳምንት የአንድነት አመራሮችን- ከድርጅቱ ካፈነገጡት ከነትእግስቱ አወል ቡድን ጋር በማከራከር ለህብረተሰቡ አንድነቶች የተከፋፈሉ ናቸው የሚል መል እክት በስፋት ያስተላለፈው ራዲዮ ፋና፤ ሀሙስ እና አርብ እለት በተመሳሳይ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትን አወያይቷል።
ይሁንና እንደ አንድነቶች ሁሉ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ያወያየው የፋና ምክትል ስራ አስኪያጅ ብሩክ ከበደ ወደ ሰማያዊ ቢሮ በመደወል <<ከኢንጂነር፡ይልቃል ጋር ውይይት ስናደርግ የነበረው ሪከርድ የሚለውን ቁልፍ ሳልጫን ነው፤ ውይይቱ ስላልተቀረጸ አይተላለፍም>> ማለቱን የሰማያዊ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ገልጿል።
<<የፋናው ጋዜጠኛ ውይይቱን ላለማስተላለፍ ሆነ ብሎ ያን ምክንያት ሲሰጥ እኛ ሁሉንም ቀርጸነው ስለነበር እኛ ጋር ስላለ እንሰጥሀለን አልነው>>የሚሉት አቶ ዮናታን፤ <<..ይሁንና ወትሮም ያን ምክንያት የሰጠው አለቆቹ በውይይቱ ሰማያዊን ለማስመታት የፈለጉትን ክፍተት ስላጡበት እንጂ ሳይቀርጸው ስለቀረ አልነበረምና -ያቀረብንወለትን ሀሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል>>ብለዋል። ራዲዮ ፋና ከቀረጸ በሁዋላ አላስተላልፍም ያለው የውይይት ፕሮግራም የተወሰነ ክፍል ኢሳት እጅ ውስጥ የገባ ሲሆን፤ በልዩ ፕሮግራም የምናቀርበው መሆኑን እናሳውቃለን።