የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር -አንድነት አባላት ላይ የተወሰደውን የጭካኔ እርምጃ በጥብቅ አወገዘ።

ጥር ፲፰(አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ትብብሩ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ ፤ገዥው ፓርቲ  በአንድነት የውስጥ ጉዳይ ገብቶ የሚፈፅመውን ደባ ለመቃወም ሰልፍ በወጡ የአንድነት አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና በፓርቲው ጽህፈትቤት ፊት ለፊት በሚገኘው ቤተ ክርስትያን አካባቢ በነበሩ አዛውንቶቸ ላይ  ሳይቀር ድብደባ በመፈጸም ፤ጭካኔውን ዳግመኛ አሳይቶናል ብሏል።

ትብብሩ ጠርቶት በነበረው የአዳር ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተወሰደውን ዘግናኝ እርምጃ ያስታወሰው መግለጫው፤<<የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር አብሮ ስለመስራትና ሌሎቹም ትብብሩን እንዲቀላቀሉ በየጊዜው የሚወተውተው አገራችን በዚህ ዘመን በማይመጥን አምባገነንና የጭካኔ ስርዓት ውስጥ የምትገኝ መሆኑን በመረዳቱ ነው፡፡>>ብሏል። <<ስርዓቱ በሰላማዊ ዜጎች ላይ አሁንም የጭካኔ እርምጃውን መድገሙ ስልጣኑን የማጣት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዳለ እና ከይስሙላ ላለፈ ለሰላማዊ ትግሉ ዝግጁ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡>> ያለው  ትብብሩ፤ <<የስርዓቱን ጨካኝነት እያወቁም ቢሆን  በራሱ በስርዓቱ የማይከበረውን ህገ መንግስታዊ መርህ ተከትለው ሰልፍ ለወጡት ቆራጥ የአንድነት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች  ትብብራችን አድናቆቱን መግለጽ ይወዳል፡፡>>ብሏል።

<< መስዋዕትነታችሁ ለነገ ድላችን ስንቅ በመሆኑ ይበልጡን ተጠናክራችሁ በጋራ ትግላችን እንደምናጠናክርም እምነታችን ነው፡፡>>ያለው ትብብሩ በተቃራኒው  ገዥው ፓርቲ ህግ የማክበርና የማስከበር ሚናውን ረስቶ በአንድነት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ የፈፀመውን ለዘመኑ የማይመጥን የጭካኔ እርምጃ በጥብቅ እናወግዛለን፡፡>>ብሏል።  <<ኢትዮጵያውያንን የማስተዳደር አቅምና ሞራል ያጣው ገዥው ፓርቲ የዜጎችን ጥያቄ በኃይል ማዳፈን የማይቻል መሆኑንና አገራችንን ወደባሰ ችግር እንደሚከታት ተረድቶ ከዚህ የጭካኔ እርምጃው እንዲቆጠብ፣ እርምጃውን የወሰዱት አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑና የታሰሩትን በአስቸኳይ እንዲፈቱ እናሳስባለን፡፡>>ብሏል ትብብሩ።

በመጨረሻም <<ፖሊስ፣ ደህንነት፣ መከላከያና ሌሎች ተቋማት ገዥው ፓርቲ አላፊ መሆኑን በመገንዘብና ከገዥው ፓርቲ ታዛዥነት በመውጣት ወገኖቻቸሁ ላይ እንዲህ አይነት የጭካኔና አሳፋሪ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥባችሁ ከህዝብ ጎን እንድትቆሙ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡>>ሲል መግለጫውን ደምድሟል።