የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን  ባዘጋጀው የዱባይ ማራቶን ኢትዮጰያውያን  በወንድም በሴትም አንጸባራቂ ድል ተቀዳጁ።

ጥር ፲፭(አስራ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአበበ ቢቂላ፣ የማሞ ወልዴና የዋሚ ቢራቱ ልጆች በአረቢያን ባህረ ሰላጤ ዳርቻ ጀግንነታቸውን አስመሰከሩ።

ወበቃማውን  የዱባይ አየርና አናት የምትበሳውን ጸሀይ በመቋቋም በደማቅ ቀለም ልዩ ታሪክ ጻፉ። የዝናም ውሀ በተጠማው የዱባይ ምድር አረንጓዴ ጎርፍ ፈሰሰ።

ዛሬ ማርፈጃውን  የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው የዱባይ ማራቶን  በወንዶች 1ኛ ኢትዮጰያ 2ኛ ኢትዮጰያ………………….12ኛ ኢትዮጵያ በመሆን አጠናቀዋል። የዱባይ ዜና አገልግሎት <<ኢትዮጰያውያኑ ዓለምን አስደነቁ>>እንዳለው፤የአባቶቻቸው ልጆች የሆኑት አንበሶቹ ማንነታቸውን፣ አቅማቸውንና ችሎታቸውን ለዓለም አሳይተዋል።ዓለምን <<ጉድ>> አሰኝተዋል።

እንደሚያሸንፍ ፈጽሞ ያልተጠበቀው ብርሀኑ ለሜ  ውድድሩን በ2 ከ05 ደቂቃ ከ28  በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፣ የ2013ቱ የዱባይና የቦስተን ሻምፒዮን ሌሊሳ ደሲሳ በ2 ሰ ዓት፣ ከ 05 ደቂቃ፤ ከ52 ሰከንድ በሁለተኛ፣ ደርቤ ሮቢ በ2ሰዓት 06፤ደቂቃ፤ 06 ሰከንድ ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል። ፈይሰል ሌሊሳ፣ሲሳይ ለማ፣ባዙ ወርቁ፣ጨለ ደቻሰ፣ግርማይ ብርሀኑ፣አዱኛ ታከለ፣አንደ ዓለምበላይ፣ዋሲሁን ላቀው እና ወርቅነህ አባተ እንደቅደም ተከተላቸው ከ4 እስከ 12ኛ በመውጣት ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

ውድድሩን እንደሚያሸንፍ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በጉዳት ምክንያት 36ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ለማቋረጥ ተገዷል። ውድድሩን በአንደኝነት ያጠናቀቀው የ20 ዓመቱ ብርሀኑ ለሜ በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ የሆነውን የ200 ዶላር  ሸልማት ሲቀበል<፣የሮጥኩት ለገንዘብ አይደለም፤ በእርግጥ አሁን በዚህ ገንዘብ ምን እንደማደርግበት እንኳ አላውቅም>> በማለት ለመገናኛ ብዘሀን አስተያያት ሰጥቷል።

ብርሀኑ አያይዞም፦የኢትዮጰያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን  ለመጪው የበጋ የዓለም ሻምፒዮና ውድድር ከመረጠው፤ ሀገሩን በማራቶን ወክሎ ለመሮጥ ዝግጁ መሆኑንም ተናግሯል። በተመሳሳይ በሴቶች በተደረገው  የማራቶን ውድድር የ2009 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የነሀስ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው አትሌት  አሰለፈች መርጊያ  ዋነኛ ተቀናቃኞቿን ኬንያውያኑን ግሊድ ኪፕሮን እና ሉሲ ካቡን በማስከተል ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቃለች።

እስከመጨረሻው  ሰዓት ድረሰ ከፍተኛ ፉክክር በታየበትና እጅግ አጓጊ በነበረው በዚህ ወድድር አሰለፈችና ኬንያዊቷ  ግሊድ አንገት- ለአንገት ተናንቀው ታይተዋል። ስታዲየሙ ገብተው ሜዳውን አብረው ከዞሩ በሁዋላ በመጨረሻዋ የመቶ ሜትር ርቀት  ማርሽ ቀያሪዋ አሰለፈች መርጊያ ተመንጭቃ በመውጣት ያሸናፊነቱን ገመድ በጥሳ ገብታለች።

በዚህም ውድድር  አንደኛ ከወጣችው ከአሰለፈች በተጨማሪ ከ4ተኛ እስከ 7ተኛ ያለውን ደረጃ የተቆናጠጡት አረንጓዴ ለባሾቹ ኢትዮጰያውያን እንስት ናቸው። አሸናፊዋ አሰለፈች የ200 ሺህ ዶላር ሽልማት ስትቀበል፤ኬንያዊቱ ግሊድ ኪፕሮስ 80 ሽህ ዶላር አግኝታለች።

በሴቶች ማራቶን  ኢትዮጰያውያን  ማንንም ጣልቃ ሳያስገቡ በተከታታይ  ሲያሸንፉ ያሁኑ  ለ9ኛ ጊዜያቸው ነው።