ጥር ፲፫(አስራ ሦስት ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሀገሪቱ የምትመራበትን ፖሊሲ ከመጠምዘዝ ጀምሮ ድርጊቱ በሀገርና በህዝብ ላይ የከፋ ተጽእኖ እንዳለው የተገነዘቡ ኢትዮጰያውያን በዩኒቨርሲቲው ላይ የተቃውሞ ዘመቻ እያስተባበሩ ነው።
አዲስ አበባ የሚገኘው ኢንተርናሽናል ሊደር ሺፕ ኢንስቲትዩት አማካይነት የሚቀርቡለትን ባለስልጣናት በአጭር ቀናት ኮርስ በማስተርስ ዲግሪ እያንሸበሸ ያለው ፤በእንግሊዝ ሀገር የሚገኘው የግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ ነው። በአይ ኤል አይ ድረገጽ እንደተመለከተው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሁሉም የሀገሪቱ ባለስልጣናት በቀናት ኮርስ ከአንድ ትምህርት ቤት ማለትም ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪ እንዲወስዱ ተደርገዋል።
እነሱም፦አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣ የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አዲሱ ለገሰ፣የቀድሞው የኮሙኒኬሽን ሚኒስትርና የ አሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ አማካሪ በረከት ስምኦን፣የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሀመድ ኡመር፣የቀድሞው የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ጁነዲን ሳዶ፣ የቀድሞው የ አዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ፣የ ኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሙክታር ከድር፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ሸፈራው ተክለማርያም፤ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን፣ የትምርት ሚኒስትር ሽፈራው ሽጉጤ፣ የሲቪል ሰርቪስ ምክትል ሚኒስትር አስቴር ማሞ፣ የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትርና የ አሁኑ የ አዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ፣የሴቶች፣ የህጻናትና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዘነቡ ታደሰ፣የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባ ኤ ካሳ ተክለብርሀን፣የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደሴ ዳልክዬ ዱካሞ፣የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አብርሐም ተከስተመስቀል፣የቀድሞ መከላከያ ሚኒስተርር ሲራጅ ፈርጌሳ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ዳውድ መሀመድ አሊ፣የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ተከስተ ረባ አያና፣በፌዴሬሽን ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሙፈሪያት ካሚል አህመድ እና በመከላከያ ሚኒስትር የምእራብ እዝ አዛዥ ሜጀር ጀነራል ብርሀኑ ጁላ ጋላቻ ናቸው።
በኢንተርናሽናል ሊደር ሽፕ ኢንስቲትዩት ድረ-ገጽ ከተዘረዘሩት ከነኚህ ባለስልጣናት ባሻገር የሀገሪቱ ጀነራሎችና የጦር አዛዦች እንዲሆም የየዞኑ የቢሮ ሀላፊዎች በሙሉ በሶስትና አራት ቀናት ኮርስ ከዚሁ ከግሪንዎች ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪ መያዛቸውን በአንድ ወቅት በዩኒቨርሲቲው መምህር የነበሩት ዶክተር ታደሰ ብሩ ይናገራሉ።
የማስተርስ ዲግሪ ከወሰዱት ከነኚህ ሹመኞች መካከል በጣት የሚቆጠሩ ጥቂቶች በራሳቸው የተማሩ ቢሆንም፤ በርካታዎቹ የ2ለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚገባ ስለማጠናቀቃቸው ትክክለኛ ማረጋገጫ ማቅረብ አይቻልም። ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከትምህርት ሚኒስትሩ ጀምሮ አሉ ለሚባሉ የሐገሪቱ ሹማምንት ሁሉ የማስተርስ ዲግሪ በዚህ መልክ መታደሉ በሀገሪቱ ፖሊሲዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ያለው ተጽ እኖ ከፍተኛ እንደሆነ ዶክተር ታደሰ ያብራራሉ።
የግሪንዊች ዩኒቨርሲቲንም “ሀገሪቱን እጅ የጠመዘዘ፣ሀገሪቱን እኪሱ ያስገባ ተቋም”ብለውታል ዶክተር ታደሰ። የትምህርት ሚኒስትሩ ዕፈራው ሽጉጤ ከዚሁ ከግሪንዊች ተቋም መመረቃቸው የሚፈጥረን የጥቅም ግጭት ዶክተር ታደሰ ሲያብራሩም፦ ይህ ድርጊት ለዩኒቨርሲቲውም እፍረት ነው፤ለሀገራችንም ጉዳት ነው ያሉት ዶክተር ታደሰ፤ የዩኒቨርሲቲውን ድርጊት ለመቃወም ፒቲሺን ፈርሞ የማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን በማውሳት፤ ኢትዮጰያውያን በተቃውሞ ዘመቻው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።