ጥር ፰(ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፖሊሶቹ በበኩላቸው – <<እኛን ህዝብ ጋር አታጣሉን>> ሲሉ ለአዛዦቻቸው ትእዛዝ ምላሽ ሰጥተዋል።
የክልሎ ፖሊሶች ከመቼውም በላይ ለእርምጃ እረንዲዘጋጁ የተነገራቸው፤የማረሚያ ቤቶችንና የትራፊክ ፖሊሶችን ጨምሮ ላለፉት ስድስት ቀናት በአማራ ክልል ለሚገኙ ፖሊሶች በሚሉ ሲሰጥ በነበረው ስልጠና ላይ ነው።
እስከ ትናንት ሐሙስ ድረስ በቆየው በዚሁ ስልጠና ላይ ከምርጫው እና ከጥምቀት በዓል ጋር በተያያዘ ሁኔታ ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመረጋጋቶችን ለማክሸፍ ዝግጁ እንዲሆኑ የታዘዙ ሲሆን፤ ተልእኳቸውን በብቃት እንዲወጡ የሚያስችላቸውን ተጨማሪ ትጥቅ ሰሞኑን እንደሚያገኙ ተነግሯቸዋል።
በባርዳር አባይ ማዶ ባለው የምክር ቤት አዳራሽ የተካሄደውን ስብሰባ የመሩት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ኮማንደር ሙሉጌታ ወርቁ እና ምክትላቸው- ፖሊሶቹን ፦<<አግዙን፤ እኛም እናግዛችሀሁዋለን>> በማለት ሲማጸኑ ሰንብተዋል።
መንግስት ከደመወዝ ጋር በተያያዘ ፖሊሶች የሚያነሱትን ጥያቄ ለመመለስ ጥረት እያደረገ እንደሆነ በመግለጽም ሰልጣኞቹን ለመደለል ሞክረዋል።
እያንዳንዱ የፖሊስ አባል መሳሪያ እንዲይዝና 240 ጥይት እንዲታጠቅ መመሪያ መተላለፉን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ጥይትና መሳሪያ ያልተሟላላቸው በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል።
እንዲሁም ከመጪው ጥር 30 እስከ የካቲት 7 ባሉት ጊዜያት የተለያዩ የመከላከያ ሀይሎች ፤ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች-ወደ ጎንደርና ባህርዳር እንደሚገቡ የገለጹት ኮሚሽነሮቹ፤ እርምጃ ለመውሰድ ከወትሮው በተለየ መልኩ በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አሳስበዋል።
ሰልጣኝ ፖሊሶቹ ባነሱት ጥያቄ፤ በአስተዳደር ችግር ህዝብ ጥያቄ ባነሳ ቁጥር ከህዝብ ጋር መጋጨት እንደማይፈልጉ በመጥቀስ፤ <<እኛ ህዝብ ጋር አንጋጪም፣ የህዝብን ቅሬታ እናንተ ፍቱ>>ብለዋል።
ለስድስት ቀናት በቆየው የባህርዳሩ ስልጠና ከደብረ ማርቆስና ከተለያዩ የክልሉ ከተሞች የመጡ ፖሊሶች የተሳተፉ ሲሆን፤ ለባህር ዳሮቹም ሆነ ከሩቅ ለመጡት አልጋንና ምግብን ጨምሮ 300 ብር ነው የተሰጣቸው።
በአበሉ ቅር ያላቸው አንድ ፖሊስ ለ ኢሳት በሰጡት አስተያየት፦<<አዛዦችና ሀላፊዎች ለተለያዩ ስብሰባዎች ሲንቀሳቀሱ ከሆቴልና ከምግብ ውጪ ለ አንድ ቀን ብቻ 250 እና 300 ብር አበል በሚያገኙበት ሀገር፤ ከሌላ ከተማ ለስልጠና መጥተው ስድስት ቀን ለቆዩ ፖሊሶች ምግባቸውንና መኝታቸውን ጨምሮ ለስድስቱም ቀን 300 ብር ብቻ መስጠት ፖሊሱን መናቅ ጭምር ነው>>ብለዋል።
በሌላ በኩል ከመጪው ማክስኞ ጀምሮ እስከ አርብ ድረስ መምህራን ስልጣና እንዲገቡ በመታዘዛቸው በባህር ዳር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንደሌለ ተነግሯል።