ጥር ፬(አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቦርዱ -አንድነት በአራት ቀናት ዉስጥ አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ አመራሮችን በምስጢር አሰጣጥ መምረጥ እንዳለበት ሲያሳስብና ሲያስጠነቅቅ መቆየቱ ይታወሳል።
ሆኖም፤ ይህን የቦርዱን ማስጥንቀቂያ ተከትሎ አንድነት ከትናንት አርብ ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤና የአመራር ምርጫ ታዛቢ እንዲልክ በደብዳቤ የተጠየቀው ምርጫ ቦርድ፤ “አየለ የሚባል ሰው ሌላ የአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ይደረጋል የሚል ደብዳቤ ስላሰገባ፣ በሁለት ቦታ መገኘት አንችልም” የሚል ምላሽ በመስጠት በጠቅላላ ጉባኤው ሳይገኝ መቅረቱን ፓርቲው ገልጿል።
አንድነት ፓርቲን የማይወክል አንድ ግለሰብ ደብዳቤ ስለጻፈ፣ ምርጫ ቦርድ በአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ አልገኝ ካለ፣ ችግሩ የምርጫ ቦርድ ነው ያለው ፓርቲው፣ ምርጫ ቦርድ ተገኝም፣ አልተገኝም፤ ጠቅላላ ጉባኤው እንደሚካሄድ ለቦርዱ በደብዳቤ ማሳወቁንም ጠቅሷል።
ምርጫ ቦርድ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ራሱን እያጋለጠና እርቃኑ እየወጣ ባለበት ወቅት፣ ከመላው አገሪቱ የተሰባሰቡ የአንድነት አባላት በጠቅላላ ጉባኤው መገኘታቸውን የጠቀሰው ፓርቲው፤ << በአራት ቀናት ዉስጥ የጠቅላላ ጉባኤ አባላትን ሰብሰበን ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት መቻላችን፤ የፓርቲያችንን ድርጅታዊ ጥንካሬም የሚያሳይ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ>>ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአንድነት ፓርቲ አባል የሆነው አቶ መሳይ ትኩ፣ ጠቅላላ ጉባኤውን ተሳትፎ ወደ ቤቱ ሲያመራ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበታል፡ አንድነት ፓርቲ በጠራው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝቶ የነበረው አቶ መሳይ ትኩ፣ ከጉባኤው ወጥቶ ወደ መኖሪያ ቤቱ በሚያቀናበት ወቅት፤ ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ በሚገኝ የኮሚኒቲ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በፖሊሶች ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመበት ገልጿል፡፡
አቶ መሳይ ትኩ፣ ባለፈው ሳምንት ‹‹አንድነትን›› ከገዢው ፓርቲ ጋር በመመሳጠር ለማፍረስ ሲሰሩ የነበሩት ግለሰቦችን ሴራ በማጋለጡ የተነሳ፤ በእነዚሁ ግለሰቦች ጠቋሚነት እና ግብረ-አበርነት በትናንትናው እለት በከባድ ሁኔታ እንዲደበደብ ምክንያት ሆኗል-ብሏል ፓርቲው።
ከግብረ-አበሮቹ መሃል ዳንኤል ሙላት የተባለው እና ቅድስተ ማርያም አካባቢ ነዋሪ የሆነው ግለሰብ ክትትል ሲያደርግበት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ምርጫ ቦርድ አንድነትና- መኢአድ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠሩ የሰጠው ቀነ ገደብ ዛሬ ሰኞ ይጠናቀቃል።አንድነት ኢሁድ እለት ጉባኤውን ቢያደርግም ቦርዱ ሰንካላ ምክንያት በመፍጠር አልተገኘም። ምርጫው ጥቂት ወራት በቀረበት ወቅት ሆነ ተብሎ እንዲፈጠር የተደረገው ውጥረት ውዴት ያመራ ይሆን?የሚለው ብዙዎችን ማነጋገሩን ቀጥሏል።