ሰማያዊ ፓርቲ የቦርዱን ውንጀላ-መሰረተ-ቢስ  አለው።

ጥር ፬(አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ታህሣሥ 28/2007 ዓ.ም ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ህገ-ወጥ ተግባራት›› እየፈጸመ እንደሆነ በመግለጽ ይቅርታ እንዲጠይቅ ለጻፈው ደብዳቤ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በፃፈው መልስ ምርጫ ቦርድ ያቀረባቸው ውንጀላቸው ህገ-ወጥ በመሆናቸው ቦርዱ ከውንጀላዎች  እንዲቆጠብ ጠይቋል፡

<< ሰማያዊ ፓርቲ ህጋዊ እውቅና ሳያገኝ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፣ ቦርዱ ያዘጋጃቸውን ስብሰባዎች ረግጦ ወጥቷል፣ ከቦርዱ እውቅና ውጭ ፓርዎቹን እያስተባበረ ነው>> በማለት ምርጫ ቦርድ  ውንጀላ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ለቦርዱ በሰጠው የደብዳቤ ምላሽ ፤ በተሻሻለው የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ምርጫ ቦርድ በሶስት ወር ውስጥ ፓርቲዎች ላቀረቡት የእውቅና ጥያቄ መልስ ካልሰጠ ማመልከቻውን ያቀረበው ፓርቲ እንደተመዘገበ እንደሚቆጠር በመጥቀስ፤ ሰማያዊ ፓርቲም ይህን ህጋዊ መሰረት ተጠቅሞ ህጋዊነቱን እንዳወጀ ገልጿል።

‹‹ድርጊታችን ህጋዊ ስለነበር ቦርዱ የህጋዊ እውቅና እና የምስክር ወረቀት ከመስጠት ውጭ በወቅቱ ምንም አይነት ውንጀላ እና ክስ አላቀረበም›› ሲልም  የአሁኑ  የቦርዱ ውንጀላ መሰረተ ቢስ መሆኑን ገልጾአል፡፡ << ሰማያዊ ፓርቲ  ቦርዱ ያዘጋጃቸውን ስብሰባዎች ለመበተን ሙከራ አድርጓል፣ ረግጦም ወጥቷል>> በማለት  ቦርዱ ላቀረበው ክስም፤  ፓርቲው ፦ቦርዱ ባዘጋጃቸው ስብሰባዎች አጀንዳዎችን አቅርቦ በቦርዱ በተደጋጋሚ ውድቅ እንደተደረገበት  በማውሳት፤ ቦርዱ ‹‹የእኔን አጀንዳ  ስሙኝ›› በሚልባቸው ስብሰባዎች ሙሉ ጊዜ የመሳተፍ፤ ግዴታም ሆነ ፍላጎት እንዳልነበረበት ገልጾአል፡፡

‹‹ባላመንንባቸው አጀንዳዎች ላይ ያለመሳተፍ ህጋዊ መብታችን ነው›› ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ወደፊትም ቢሆን ቦርዱ በተመሳሳይ አቀራረብና ይዘት የሚቀጥል ከሆነ ስብሰባዎችን እየጣለ እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡
‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ከቦርዱ እውቅና ሳያገኝ ትብብር የሚባል አደረጃጀት መስርቶ ህገ-ውጥ እንቅስቃሴ አድርጓል›› በማለት ለቀረበበት ክስ ሰማያዊ በሰጠው ምላሽ-በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝባ አዋጅ 573/2000 32፣ 34ና 35 ውህደት፣ ቅንጅትና ግንባር ካልሆነ በስተቀር ፓርቲዎች በሚያግባቧቸው ጉዳዮች ተባብረው ሲሰሩ የምርጫ ቦርድ እውቅናን መጠየቅ እንደማይጠበቅባቸው ጠቅሶ፣ ቦርዱ የፓርቲዎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ ህጋዊ መብትን እየተጋፋ መሆኑን አውቆ ከእንደዚህ አይነት ውንጀላዎች እንዲቆጠብ ጠይቋል፡፡
<<በአጠቃላይ ምርጫ ቦርድ፦ ‘ሰማያዊ ፓርቲ ይቅርታ ይጠይቅ’ ብሎ ያቀረባቸው ክሶች መሰረተ- ቢሶችና ህጋዊ መሰረት የሌላቸው በመሆናቸው ተቀባይነት የላቸውም>>ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤  ‹‹ይህ አይነት የይቅርታ ጠያቂና- ይቅርታ አድራጊ ግንኙነት ለምርጫ ቦርድ በህግ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት ውጭ ከመሆኑም በላይ፤ የቦርዱንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ህጋዊ ግንኙነት ያልተከተለ ሰለሆነ፤ ተቀባይት የሌለው መሆኑን እንገልጻለን›› ሲል ይቅርታ ጠይቅ መባሉ ህገ-ወጥ መሆኑን ገልጾአል፡፡