ጥር ፩(አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ስኞ እለት ታህሳስ 27 ቀን 2007 ዓመተ ምህረት ታንኮችን የጫኑ የመከላከያ ሰራዊት ተሽከርካሪዎች ባህር ዳር ከተማ መግባታቸውን የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል።
የከተማው ነዋሪዎች ለኢሳት እንዳሉት፤ ከየት አቅጣጫ እንደመጡ ያልታወቁ የጦር ተሸከርካሪዎች ሰኞ ምሽቱን ባህርዳር ወደሚገኘው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት(መኮድ) ካምፕ ገብተው ካደሩ በሁዋላ በማግስቱ ጧት ወደ ጎንደር አቅጣጫ ተጓጉዘዋል።
ተሸከርካሪዎቹ የጫኗቸው ታንኮች ላይ ከባድ መሳሪያዎች እንዳልተጠመደባቸው የሚናገሩት የዓይን ምስክሮች፤ ታንኮቹ እግረኞችን ለመምታት የሚያገለግሉ እንደ ዲሸቃ ያሉ ቀላል መሳሪያ የሚተኮስባቸው ናቸው ብለዋል።
ከጦር ተሽከርካሪዎቹ በተጓዳኝም በአውቶቡሶች የተጫኑ ወታደሮችም አብረው መጓጓዛቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ሰሞኑን በጎንደር አርማጭሆ “ሶረቃ” የሚባለውን አካባቢ ወደ ክልል አንድ ለማካለል በታጣቂዎች የተደረገው ሙከራ በአካባቢው ህዝብ ተቃውሞ እንደከሸፈና ክስተቱን ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት ከሁለቱም ወገን በርካቶች እንደተጎዱ መዘገባችን ይታወቃል። መንግስት ሰሞኑን በተለያየ አቅጣጫ ወደ ሰሜን ኢትዮጰያ የጦር ተሸከርካሪዎችን እያጓጓዘ ነው።