ታኀሳስ ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በምርጫ 97 ወቅት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የሸለመው “ያራ” የተሰኘ የኖርዌይ ድርጅት በሙስና ተከሰሰ ፤ ኢትዮጰያውያንም ተጨማሪ ክስ ያቀርባሉ።
በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1997 ዓመተ ምህረት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ 200 000 ዶላር የሸለመውና- ሽልማቱን ተከትሎ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የኢትዮጵያ ብቸኛ የማዳበሪያ አቅራቢ የሆነው የ”ያራ ኩባንያ”ዳይሬክተር ቶርሊፍ ኢንገር፤ በኖርዌይ ታሪክ ትልቅ በተባለው የሙስና ክስ ነገ ጠዋት ኦስሎ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ። የያራ ዳይሬክተር የተከሰሱት፤ በህንድ እና ሊቢያ ከማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሙስና እንደሆነ ተመልክቷል።
“ያራ ኩባንያ” በእነዚህ ሁለት ሃገራት ውስጥ ባልተገባ መልኩ ጨረታ አሸንፎ ማዳበሪያ የማቅረብ ኮንትራት ያገኘው፦ ዳይረክተሩ ከጨረታው በፊት ለሁለቱ ሃገራት ባለሥልጣኖች 8 ሚሊዮን ዶላር በመስጠታቸው መሆኑን የኖርዌይ የዜና አገልግሎት (NRK) ዘግቧል።
እንደ ኤን. አር ኬ ዘገባ፣ የ71 አመቱ ቱርላይፍ ኤንገን ጥፋተኛ ሆነው ከተገ፤ የቀረውን ህይወታቸውን በእስር ቤት ያሳልፋሉ። በሰኔ ወር 1997 ዓመተ ምህረት በኢትዮጰያ ታጣቂዎች ከምርጫው ጋር ተያይዞ ተቃውሞ ያሰሙ ንጹሀንን በገደሉ ማግስት የአሁኑ ተከሳሽ የያራ ኩባንያ ዳይሬክተር- “የምግብ ምርትን በመጨመርና ድህነትን በመቀነስ ላደረጉት አስተዋጽኦ በሚል” ለአቶ መለስ ዜናዊ የ 200 ሺህ ዶላር ሽልማት ማበርከታቸው ይታወሳል። “ያራ” ለአቶ መለስ ሽልማቱን ባበረከተ በጥቂት ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ ማዳበሪያ ለማቅረብ የወጣውን ጨረታ እንዲያሸንፍ የተደረገ ሲሆን፤ በጨረታው ስምምነት፦ ከገቢው 30 በመቶው <<ኢፈርት>> ተብሎ ለሚጠራው የህወሀት ካምፓኒ የሚተላለፍ ሆኖ ቆይቷል።
ይህ ከሆነ ከሰባት ዓመታት በሁዋላ ነው “ያራ” በሊቢያና በህንድ ከማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በ8 ሚሊዮን ዶላር ሙስና ክስ የተመሰረተበት።ይህን ክስም ተከትሎ በምእራብ ኖርዌይ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጰያውያን “ያራ” በኢትዮጰያ ማዳበሪያ አቅራቢ ለመሆን ያሸነፈበት መንገድ በኖርዌይ አቃቤ ህግ እንዲመረመርና እንዲጣራ ተጨማሪ ክስ ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል።