ኀዳር ፬(አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ የዕንቁ መፅሔት አዘጋጅ በነበረው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ላይ የተሳሳተ መረጃን በመስጠት፣ ማነሳሳትና ግዙፍ በሆነ ማሰናዳት ወንጀል የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል አራዳ ምድብ ችሎት ህዳር 2 ቀን 2007 ዓ.ም ክስ
የመሠረተበት ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ የተጠየቀውን የ20ሺህ ብር ዋስትና ማቅረብ ባለመቻሉ በቂሊንጦ በእስር ላይ መሆኑ ታውቆአል፡፡ የጋዜጠኛውን ዋስትና በመዋጮ ለመሸፈን የቅርብ ጉዋደኞቹ የባንክ አካውንት በመክፈት በዛሬው ዕለት ዕርዳታ ማሰባሰብ ጀምረዋል፡፡
የዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር እንደሚያስረዳው የቀድሞ የዕንቁ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፤ አቶ አምሳሉ ገ/ኪዳን በተባሉ ፀሐፊ “የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት ሀውልቶች የነማን እና ለነማንስ ናቸው?”
በሚል ርዕስ ባቀረበው ፅሁፍ መነሻነት፤ ባሳለፍነው ዓመት በጅማ ዩኒቨርስቲ በሚገኙ ተማሪዎች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ መንስዔ መሆኑንና በግጭቱም 30ሺህ ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ይጠቅሳል።
ጋዜጠና ኤልያስ ማክሰኞ ዕለት ክሱን ለመስማት ፍ/ቤት በተገኘበት ወቅት የ20 ሺ ብር ዋስትና አቅርቦ እንዲለቀቅ ፍ/ቤቱ ብይን የሰጠ ቢሆንም ጋዜጠኛው ለጊዜው የሚያሲይዘው ገንዘብ በማጣቱ ቀጨኔ መድሃኒያለም አካባቢ በሚገኝ አንድ ፖሊስ ጣቢያ እንዲያድር ከተደረገ በኃላ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መዛወሩ ታውቆአል፡፡
የጋዜጠኛው የቅርብ ጉዋደኞችና ወዳጆች ጋዜጠኛውን ከእስር ለማስፈታት የባንክ አካውንት በመክፈት ዕርዳታ ማሰባሰብ መጀመራቸውንና የአካውንቱ ቁጥርም
የኢትዮጽያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር 1000097440655
Swift Code:- CBETETAA መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ፍ/ቤቱ የጋዜጠኛውን ጉዳይ ለማየት ለታህሳስ 4 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡