ጥቅምት ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሶማሊ ክልል በፕሬዚዳንቱና በ7 የስራ አስፈጻሚ አባላት መካከል ተፈጥሮ የቆየውን ውዝግብ ለመፍታት ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሁሉንም ወገኖች አዲስ አበባ ቢጋብዙም፣ ፕሬዚዳንቱ አቶ አብዲ ሙሃመድ የጠ/ሚሩን ጥሪ
ውድቅ በማድረግ የራሳቸውን ጉባኤ በመጥራት አዲስ የስራ አስፈጻሚዎችን ሾመዋል። ባለፈው መስከረም 24 ቀን በፊቅ ከተማ በተደረገው ጉባኤ፣ ፕሬዚዳንቱ የራሳቸውን ደጋፊዎችና ዘመዶቻቸውን በስራ አስፈጻሚነት አስመርጠዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ እናገኛለን
ብለው ተስፋ ያደረጉት ከክልሉ የተባረሩት 7 ስራ አስፈጻሚዎች አሁንም በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግስት ባለስልጣናትን እየተማጸኑ ነው።
ቀደም ብሎ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝና የደህንነቱ ሹም በአንድ ወገን፣ የምስራቅ እዝ ሃላፊ ሆኑት ጄኔራል አብርሃ በቅጽል ስማቸው ካታር አቶ አብዲን ደግፈው በሌላ ወገን ሆነው ሲፋለሙ ከቆዩ በሁዋላ ፣ አቶ አብዲ መሃል ላይ ያሉትን የፌደራል ሹሞፐች በገንዘብ በመደለል
ለማሸነፍ መቻላቸውን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የኢሳት የሶህዴፓ የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።
ፊቅ ላይ ተደርጎ በነበረው ጉባኤ ላይ ከፌደራል መንግስት የአጋር ድርጅቶች ተወካይ የሆኑት አቶ አማኑኤል አብርሃ፣ ቀድሞ ክልሉን በአማካሪነት ስም ሲመሩ የነበሩት የህወሃቱ አቶ ተወልደ በርሄ ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ምክትል ዲኤታ አቶ ማሀመድ ሽዴ እንዲሁም የፌደሬሽን
ምክር ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሀመድ ረሺድ ተገኝተዋል።
ልኡኩን በመምራት የተገኙት አቶ አማኑኤል አብርሃም ከፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ ገንዘብ በጉቦ መልክ እንደተቀበሉ የሚገልጹት ምንቾች፣ ቀድሞ የነበራቸውን አቋም በመቀየር የፕሬዚዳንቱ ደጋፊ ሆነዋል። በከፍተኛ ሙስና የሚወነጀሉት ጄ/ል አብርሃ፣ አቶ አብዲ ከወረደ ክልሉ ከቁጥጥር
ውጭ እንደሚሆን ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።
የፊቁን ጉባኤ ተቃወሙት ጠ/ሚንስትሩና የደህንነት ሃላፊው አቶ ጌታቸው አሰፋ ጉባኤው ህገወጥ ነው በሚል እንደገና እንዲረግ ቢጠይቁም፣ ጄ/ል አብርሃና ሌሎች ከማእከል የተላኩት ባለስልጣናት ከአቶ አብዲ ጎን በመቆማቸው ኢህአዴግ ለሁለት መከፈሉን ለማወቅ ተችሎአል።
አቶ አብዲ ስልጣናቸውን እያጠናከሩ በመምጣት ላይ ሲሆኑ፣ ካቢኔያቸውን ካዋቀሩ በሁዋላ በባንዲራ ቀን አሳበው ተቃዋሚዎቻቸውን ለማሸማቀቅ አዲስ አበባ መግባታቸውን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
የአቶ አብዲ በስልጣን መቆየት የጠ/ሚንስትሩን ስልጣን አልባነትና አሁንም ስልጣኑ በወታደራዊ አዛዦች መያዙን የሚያመልክት ነው የሚሉ አስተያየቶችም ይቀርባሉ።
አቶ አብዲ ” እኔ እንደማንኛውም ባለስልጣናት ጥቅም ላይ ውየ የምጣል ኮንዶም አይደለሁም” ብለው መናገራቸውንም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ይገልጻሉ።