ሐምሌ ፰(ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሃማስና በእስራኤል መካከል የተጀመረው ጦርነት ፣ በግብጽ አደራዳሪነት ለሰአታት ጋብ ብሎ የቆየ ቢሆንም፣ እስራኤል ድብደባውን እንደገና መጀመሯን ቢቢሲ ዘግቧል።
በግብጽ የቀረበውን የሰላም ስምምነት እስራኤል ብትቀበለውም፣ ሃማስ ግን ስምምነቱ ሽንፈትን እንደመቀበል ይቆጠራል በሚል ሳይቀበለው ቀርቷል።
ይህን ተከትሎም እስራኤል የአየር ድብደባውን እንደገና ጀምራለች። እስካሁን በደረሰው ጥቃት ከ192 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል፤ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩትም ቆስለዋል። በእስራኤል በኩል 4 ሰዎች በሃማስ ሮኬት መቁሰላቸው ታውቋል።
እስራኤል በምትሰነዝረው ወታደራዊ ጥቃት የሞቱት አብዛኞቹ ሲቪሎች መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል። እስራኤል ግን መረጃውን ታስተባብላለች።