የካቲት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መስሪያ ቤቱ በ2013 ሪፖርቱ በአገሪቱ የሚታዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በዝርዝር አስቀምጧል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታዩት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካከል ሃሳብን በነጻነት የመግልጽና የመደራጀት መብት ቀዳሚ መሆኑን ሪፖርቱ ይገልጻል።
ዜጎች በዘፈቀደ ይታሰራሉ፣ ይታፈናሉ፣ በእስር ቤት ይሰቃያሉ፣ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ይገደላሉ፣ በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ማስፈራሪያ ይደርስባቸዋል እንዲሁም በእስር ቤት ውስጥ አሰቃቂ ድርጊቶች ይፈጸሙባቸዋል።
ፍርድ ቤቶች በመዳከማቸው የፖለቲካ ፍለጎት ማስፈጸሚያ መሳሪያ መሆናቸውን፣ ዜጎች መንግስትን የመለወጥ እድላቸው አነስተኛ መሆኑን፣ ፖሊስ፣ አስተዳደርና ፍርድ ቤቶች በሙስና የተዘፈቁ በመሆናቸው ተጠያቂነት ያለበት ስርአት ማስፈን አለመቻሉን ሪፖርቱ ያስረዳል።
በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ቁልቁል የፍጢኝ ታስረው የውስጥ እግራቸው እንደሚገረፍ፣ በውሃ ውስጥ እየገቡ እንዲሰቃዩ እንደሚደረግ፣ በእስር ቤት ውስጥ ድብደባ መፈጸምና ለህይወት አስጊ በሆነ እስር ቤት ውስጥ እንዲቆዩ በማድረግ መቅጣት በኢትዮጵያ የተለመደ ነው ብሎአል።
ከልካይ የሌለበት የሶማሊ ክልል ልዩ ሚሊሺያም ዜጎችን እንደፈለገ እንደሚገድልና እንደሚያስር፣ በክልሎች ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ልዩ ሚሊሺያዎችም እንዲሁ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጉዳይ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን አትቷል።
ከሁለት አመት በፊት ባለው አሃዝ በ6የፌደራልና በ120 የክልል እስር ቤቶች ከ70 እስከ 80 ሺ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ወንጀሎች መታሰራቸውን የገለጸው ሪፖርት፣ በይፋ የማይታወቁ በጦር ካምፖች ውስጥ ያሉ እስር ቤቶችንም ዘርዝሯል። ደዴሳ፣ ብር ሸለቆ፣ ጦላይ፣ ሆርማት፣ ብላቴ፣ ታጠቅ፣ ጅጅጋ፣ ሆለታና ሰንቀሌ ስውር እስር ቤቶች ተብለው ተጠቅሰዋል።
የኢድ አል ፈጥር በአልን ለማክበር በስታዲየም ላይ ተገኝተው በነበሩ ሙስሊሞች ላይ መንግስት በወሰደው እርምጃ ከታሰሩት ወደ 1 ሺ ከሚጠጉት ሰዎች መካከል የተወሰኑት በእስር ቤት ውስጥ መሞታቸውንም ሪፖርቱ ጠቅሷል።
የሙስሊም ጉዳዮች መጽሄት አዘጋጅ ሰለሞን ከበደ በእስር ቤት ውስጥ ድብደባ እንደተፈጸመበት የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት አለሙ፣ በ አንዱአለም አራጌ፣ ኦባና ሊሌሳ፣ በቀለ ገርባና ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች ላይ እየደረሱ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንዲሁም በሴቶችና ህጻናት ላይ ስለሚደርሱ የመብት ጥሰቶች፣ በአናሳ ጎሳ አባላት ላይ ስለሚደረሰው መፈናቀልና ግጭት በዝርዝር አስቀምጣል።
የአሜሪካ ምክር ቤት የኢትየጵያ መንግስት የሰብአዊ መብቶች አያያዙን እስከሚያከብር ድረስ የ2014 እርዳታ እንዳይሰጥ ህግ ማውጣቱ ይታወቃል። የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ደረስ በዚህ ህግ ዙሪያ የሰጠው አስተያየት የለም።