አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ክብረ-ወሰን ሰበረች።

ጥር ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በስዊድን-ስቶኮሆልም በተካሄደው የቤት ውስጥ የ 3 ሺ ሜትር ውድድር አትሊት ገንዘቤ ዲባባ በአስደናቂ ብቃት በማሸነፍ  አዲስ የዓለም ክብረወሰን አስመዘገበች።

ገንዘቤ ዲባባ ርቀቱን በ8:ደቂቃ 16 ሴኮንድ  60 ማይክሮ ሴኮንድ በማጠናቀቅ  እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2007 ዓመተ ምህረት፣ ማለትም ከ 7 ዓመት በፊት  በአገሯ ልጅ በአትሌት መሰረት ደፋር  ተይዞ የነበረውን ሪከርድ ከ7 ሰከንድ በላይ አሻሽላለች።

ይህ ሰዓት ከ1993 ዓመተ ምህረት ወዲህ  በቤትም ሆነ ከቤት ውጪ በተደረጉ የ 3000 ሜትር ውድድሮች በጣም ፈጣኑ ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል።

ገንዘቤ ከ አምስት ቀን በፊት በተካሄደ የቤት ውስጥ የ 1500 ሜትር ውድድር በተመሳሳይ መልኩ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ጨብጣለች።