የዩክሬንን የውስጥ ቀውስ አስመልክቶ የ አሜሪካ ባለስልጣናት የአውሮፓ ህብረትን ሲዘልፉ የሚደመጡበት የስልክ ምልልስ አፈትልኮ ወጣ።

ጥር ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የዩናይትድ ስቴስት ከፍተኛ  ዲፕሎማት የሆኑት ምክትል ሴክሬታሪ  ቪክቶሪያ ኑላንድ- በዩክሬን ከ አሜሪካ አምባሳደር ጋር ስለ ዩክሬን ግጭት በስልክ ያወሩት ወሬ  ተጠልፎ በድረ ገፆች መለጠፉ አሜሪካን ማሳፈሩን ዘገባዎች አመልክተዋል።

ቪክቶሪያ ኑላንድ  በዙሁ የስልክ ምልልስ ላይ ስለዩክሬን ግጭት ሲያወሩ የአውሮፓ ህብረትን ሲወቅሱና  በወረደ ቃላት ሲዘልፉ ይሰማሉ። በሁኔታው የደነገጠችው አሜሪካ ፦”ቪክቶሪያ ኑላንድ ለተናገሩት ነገር ይቅርታ ጠይቀዋል” ስትል ፈጥና አስተባብላለች።

በዩክሬን የተቀሰቀሰው ያለመረጋጋት ያከትም ዘንድ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት   የሀገሪቱን ፓርቲዎችን ለማስማማት  ጣልቃ  መግባታቸው ይታወቃል።

ባለፈው ህዳርወር መጨረሻ ላይ  ፕሬዚዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች ከአውሮፓ ህብረት ጋር የትብብርና  የንግድ ስምምነት ለመፈረም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ በዩክሬን የተነሳው ህዝባዊ አመጽ እስካሁን ሊበርድ አልቻለም።

ዩክሬን ስምምነቱን እንዳትፈርም  ጣልቃ ገብታ ጫና የፈጠረችው ሩሲያ ናት ።ሩሲያ በበኩሏ አሜሪካንና የአውሮፓ ህብረትን በጣልቃ ገብነት ትወነጅላለች። የአሁኑ የስልክ ጠለፋ  በሩሲያ ሳይካሄድ እንዳልቀረ አሜሪካ እየገለጸች ነው።