የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች 2 የኦብነግን መሪዎች አፍነው መውሰዳቸውን ግንባሩ ገለጸ

ጥር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር ለኢሳት በላከው መረጃ ከመንግስት ጋር ለመደራደር ኬንያ የሚገኙት የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ሱሉብ አህመድና አሊ ሁሴን በኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ታፍነው ወደ አልታወቀ ቦታ ተወስደዋል። መሪዎቹ የታፈኑት ናይሮቢ ውስጥ ሲሆን፣ ከመንግስት ጋር ለሚደረገው ሶስተኛ ዙር ውይይት ዝግጅት እያደረጉ ነበር።

ግንባሩ በመግለጫው ከዚህ ቀደምም የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የኦብነግ መሪዎችን ሲገድሉና ሲያፍኑ ነበር ብሎአል። በፈረንጆች አቆጣጠር በ1998 5 የኦብነግ አመራሮች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ድርድር ሲያካሂዱ ከቆዩ በሁዋላ 3ቱ ሲገደሉ 2ቱ ደግሞ ተጠልፈው ተወስደዋል። ከሁለት አመት በፊት ደግሞ የግንባሩ ከፍተኛ አመራር ናይሮቢ ውስጥ ተገድሏል።

ግድያው ከመንግስት ጋር የሚደረገውን ቀጣይ ድርድር እንደሚያበላሸው የገለጸው ኦብነግ፣  ይህ የፈሪዎች ድርጊት የኦጋዴን ህዝብ ለነጻነቱ ይበልጥ መቆም እንዳለበት የሚያስገነዘብን ነው ሲል አክሏል።

ግንባሩ ሁለቱ ሃይሎች እንዲደራደሩ ሁኔታዎችን ያመቻቸው የኬንያ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ሰዎቹ እንዲለቀቁ እንዲያደርግ ጠይቋል።