ነጋዴዎች ቦንድ እንዲገዙ እየተገደዱ ነው

ጥር ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በወልድያ የሚገኙ ነጋዴዎች፣ ለኢሳት እንደገለጹት  ፈቃድ ለማሳደስ በሚሄዱበት ጊዜ ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ቦንድ ካልገዛችሁ አይታደስላችሁም ተብለዋል። የግል ክሊኒኮችን ከፍተው የሚሰሩ ነጋዴዎች ለኢሳት እንደገለጹት፣ ፈቃዳቸውን ለማሳደስ በሚሄዱበት ጊዜ ከ2ሺ ብር ጀምሮ ቦንድ እንዲገዙ ተገደዋል። የኢህአዴግ ካድሬዎች በየቀበሌው እየዞሩ ነጋዴዎች ቦንድ እንዲገዙ ያለበለዚያ የንግድ ፈቃዳቸው እንደማይታደስላቸው እያስጠነቀቁ ነው።

እድሮችና  እቁቦችም በተመሳሳይ መንገድ ቦንድ እንዲገዙ እየተገደዱ ነው። ለአባይ ግድብ ግንባታ በሚል መምህራንና የመንግስት ሰራተኞች ያለፍላጎታቸው ከደሞዛቸው ላይ የሚደረገውን መዋጮ እየተቃወሙት ነው።

ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀው የግድቡ ግንባታ ከግብጽ በኩል ተቃውሞ እየገጠመው ቢገኝም የኢትዮጵያ መንግስት ህዝቡን አንድ በማድረግ የሚመጣውን ተጽእኖ ለመቋቋም እርምጃ ሲወስድ አለመታየቱን ታዛቢዎች ይናገራሉ። ዘጋቢያችን ከወልድያ ያነጋገራቸው አንዳንድ ሰዎች እንደገለጹት መንግስት ግድቡን ለመገንባት ከህዝብ የሚፈልገውን ያክል መዋጮ ለማግኘት አልቻለው አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ባለመቻሉ ሲሆን፣ በግብጽ በኩል ሊመጣ የሚችለውን ማንኛውንም አደጋ መቋቋም የሚቻለውም ህዝቡን አንድ ለማድረግ ብሄራዊ መግባባት መፍጠር ሲችል ብቻ ነው ብለዋል።

አንድ የግብጽ ጋዜጣ የመስኖ ሚኒስትሩን ጠቅሶ ” ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታ 30 በመቶ ደርሷል በማለት የምታስወራው ለፖለቲካ ፍጆታ መሆኑንና ፕሮጀክቱን ለመጨረስ የገንዘብ እጥረት ማጋጠሙን” ዘግቧል። በሌላ በኩል ግን የግብጽ ጠ/ሚንስትር ወታደራዊ አዛዦችንና ፖለቲከኞችን  በመሰብሰብ በግድቡ ዙሪያ ስለሚወስዱት እርምጃ አወያይተዋቸዋል።