በኦሮሚያ ካሉ ከ2 መቶ በላይ የአበባ ልማት ባለሃብቶች የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ማረጋገጫ የወሰዱት ከ10 አይበልጡም ተባለ፡፡

ጥር ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦሮሚያ የአካባቢ ጥበቃ የአካባቢ ተፅዕኖና ግምገማ መምሪያ ኃላፊ አቶ አሕመድ ሁሴን በኦሮሚያ ክልል አካባቢን ለመጠበቅ እየተደረጉ ስላሉ እንቅስቃሴዎችና አካባቢን በማይጠብቁት ላይ ምን ዓይነት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት እንዲሁም ስለተወሰዱ እርምጃዎች እንደገለጹት፣  በኦሮሚያ ክልል ከአካባቢ ተፅዕኖ ጋር የሚነሱ ችግሮች በክልሉ በሚካሄዱ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የተነሳ በአካባቢ ላይ ጉዳት ይደርሳሉ፡፡

ይህንን ጉዳት ለመቀነስ አንድ ፕሮጀክት ከመተግበሩ በፊት በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ተገምግሞ ለችግሮች መፍትሄ የሚጠቆምበት ዘዴ ይቀየሳል ያሉት ባለስልጣኑ፣ ይሁን እንጅ በክልሉ በሚካሄዱ ልማቶች የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ በጎላ መልኩ እየተካሄደ  አይደለም ብለዋል፡፡

ይህም ከባለሃብቶች ግንዛቤ ማነስ ሳይሆን የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናቱ ተጨማሪ በጀትና ጊዜ ስለሚጠይቅ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡ ” በዚህ ክልል ከፍተኛ የአበባ ልማት የሚካሄድ በመሆኑ በአካባቢ ላይ ተፅዕኖ እንደሚመያመጣ የገለጹት ሃላፊው፣ በተለይ የውኃ ብክለትን ለመቀነስ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ካሉ ከ2 መቶ በላይ የአበባ ልማት ባለሃብቶች የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ማረጋገጫ የወሰዱት ከ10 አይበልጡም፡ የሚሉት ሃላፊው፣   በፌዴራል ደረጃ አዋጅ ቢወጣም በክልል ደረጃ የወጣ የህግ ባለመኖሩ ግምገማውን ለማድረግ አላስቻለም፡፡  በክልል ደረጃ የበለጠ ጠንከር ያለ ሕግ ለማውጣት እየሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

እንደ ሌሎች የአገራችን ክፍሎች ሁሉ በዚህም ክልል የተፈጥሮ ሃብቶች ላይ አደጋ መድረሱን የገለጹት አቶ አህመድ ፣  በመሥሪያ ቤቶች መካከል ተባብሮ አለመሥራት የፈጠረው ክፍተትም ችግሩን እንዳባባሰው ተናግረዋል።