ታህሳስ ፲፮( አስራ ስድስት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው ረቡዕ ቦር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የታየውን ከፍተና ግጭት ተከትሎ በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አልታወቀም። በርካታ ደቡብ ሱዳናውያን በመንግስት ደጋፊና ተቃዋሚዎ ታጣቂዎች መገደላቸውን ሲኤን ኤን የዘገበ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚኖሩ ከ1 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን እጣ ፋንታ እስካሁን በውል አለመታወቁንም ከአካባቢው ሸሽተው ወደ ኡጋንዳ ድንበር የደረሱ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያኑ እንደሚናገሩ በአካባቢው ያለው ሁኔታ እጅግ አስፈሪ ነው። ኡጋንዳና ኬንያ በቦር ያሉ ዜጎቻቸውን መኪናዎችን ልከው ሲያስወጡ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ዝምታ መምረጡ በእጅጉ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል
በሌላ ዜና ደግሞ ሁለቱን ተዋጊ ሀይሎች ለመሸምገል የኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝና የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጁባ ተገኝተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሀኖም እንደገለጹት ሁለቱም መሪዎች ከፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ጋር ግልጽ ውይይት አድርገዋል:፡ ይሁን እንጅ ሁለቱም ሀይሎች መቼ የተኩስ አቁም ስምምነት አድረገው ወደ ሰላሙ ጠረጴዛ እንደሚመለሱ ግልጽ አላደረጉም። የአውሮፓ ህብረትም ልኡኩን ወደ አካባቢው ልኳል። ቻይናም በበኩሏ የልኡካን ቡድኗን ወደ አካባቢው እንደምትልክ አስታውቃለች።