ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ሕዝብ ያዋጣው 5.7 ቢሊየን ብር ነው ተባለ

ታህሳስ ፲፮( አስራ ስድስት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም  ኢሳት ዜና :-ባለፉት ሶስት ዓመታት ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ከሕዝብ የተዋጣው ገንዘብ ከ10 ቢሊየን ብር በላይ መሆኑ በመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ሲነገር ቢቆይም አንድ ባለስልጣን ግን ትክክለኛው አሀዝ  5 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ጽ/ቤት የአቶ በረከት ስምኦን ምክትል የሆኑት አቶ ዛዲግ አብርሃን ጠቅሶ መንግስታዊው አዲስ ልሳን ጋዜጣ እንዳሰፈረው ባለፉት ሶስት ዓመታት ከህዝብ
የተዋጣው ገንዘብ 5 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ብቻ ነው፡፡

የዋጋ ግሽበትን ሳይጨምር ከ85 ቢሊየን ብር ባላይ ይፈጃል የተባለው የአባይ ግድብ ግንባታ ማከናወኛ ሕዝቡ እስካሁን ማዋጣት የቻለው ገንዘብ መጠን አነስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ቃል የገቡ በርካታ ባለሃብቶች በቃላቸው መሰረት መዋጮውን አለማስገባታቸው ትልቅ ችግር መሆኑ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች አመልክተዋል፡፡

የመንግስት ሠራተኞችና ሌሎች ደመወዝተኞች ገንዘቡ ከደመወዛቸው የሚቆረጥ በመሆኑ በትክክል መክፈል የቻሉት እነዚሁ ወገኖች ብቻ ናቸው ተብሎአል፡፡ይህም ግድቡ በተያዘለት የጊዜ ገደብ መሰረት ለማጠናቀቅ የፋይናንስ ችግር ማነቆ ሊሆን እንደሚችል
ከወዲሁ የሚያመላክት ሆኖአል፡፡

በተያያዘ ዜና ከአባይ ግድብ ጋር በተያያዘ በግዳጅና በፍላጎት ከሕዝብ የሚሰበሰብ ገንዘብ ለታቀደለት ኣላማ በትክክል ስለመዋሉ የሚያረጋግጥ ግልጽ የሆነ አሰራር በመንግስት በኩል እስካሁን አለመዘርጋቱ አሳሳቢ መሆኑን ለጉዳዩ ቀርበት ያላቸው ወገኖች አስታውቀዋል፡፡

ሕዝቡ ከደመወዙ በግዳጅና በፍላጎት ቦንድ እንዲገዛ ሲደረግ መቆየቱን ያስታወሱት እነዚሁ ወገኖች ሕዝቡ ምንያህል በመዋጮ መልክ እንደተሰበሰበና በምን መልኩ ስራ ላይ እየዋለ እንደሆነ የተረጋገጠ መረጃ አለመያዙ አሳሳቢ ነው ተብለዋል፡፡

የስርዓቱ ቁንጮዎች ከላይ እስከታች በሙስናና ብልሹ አሰራር ውስጥ መዘፈቃቸውን በተረጋገጠበት በዚህ ወቅት ከህዝብ የሚሰበሰብ ገንዘብ በትክክል ስራ ላይ ይውላል ብሎ ለመገመት አዳጋች መሆኑን የጠቆሙት እነዚሁ ወገኖች መንግስትም ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልክ የሕዝብ ገንዘብ ስለማስተዳደሩ ማረጋገጫ እያቀረበ አለመሆኑ አሳሳቢ ነው ሲሉ አክለዋል።

ግድቡ በመጋቢት ወር 2003 ዓ.ም በይፋ የመሰረት ድንጋ ተጥሎ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ የመንግስትና የግል ሰራተኞች፣ባለሃብቶችና ሌሎች ወገኖች ገንዘብ ሲያዋጡ መቆየታቸውን ያስታወሱት እነዚሁ ወገኖች ሌላው ቀርቶ የቦንድ ሰርተፊኬት ያገኙ ሰራተኞች ቁጥር ብዙ አለመሆኑና ገንዘቡም በትክክል መቼ እንደሚመለስ አለመታወቁን አስታውሰዋል፡

፡ከምንም በላይ ሳይወድ በግድ ያዋጣው ሰፊ ሰራተኛ ገንዘቡ በትክክል ስራ ላይ እየዋለ መሆኑን እንኩዋን የሚያውቅበት መንገድ አለመኖሩ የስርዓቱ ቁንጮዎች የሕዝብን ገንዘብ በግልጽ ለማስተዳደር ፍላጎት እንደሌላቸው የሚሳይ ነው ብለዋል፡፡

የግድቡን አብዛኛውን ስራዎች የሚሰሩት ሳሊኒ የተባለው የጣሊያን ኩባንያና የህወሀት እንዲሁም ከህወሀት ጋር በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው ድርጅቶች ናቸው። በመከላከያ ስም ከፍተኛ የህወሀት ጄኔራሎች የሚያንቀሳቅሱት እና ከፍተኛ ሙስና እንደሚፈጸምበት የሚነገርለት ሜቴክ እየተባለ የሚጠራው ድርጅት በግንባታው ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ ነው። የወ/ሮ አዜብ መስፍን የቅርብ የስጋ ዘመድ የሆኑት ግለሰብ ንብረት የሆነው ወርኪድ የተባለው ድርጅትም እንዲሁ በእቃዎችና በማሽነሪ አቅርቦት በኩል ከፍተኛ ስራዎች ተሰጥቶት እየሰራ ነው።