ህዳር ፳፯(ሃያ ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ደቡብ አፍሪካውያን ለነፃነት አባታቸውና ለቀድሞ መሪያቸው ለኔልሰን ማንዴላ ሀዘናቸውን ለመግለጽ ወደ ጁሀንስበርግበና ሶዌቶ እየተሰበሰቡ ሲሆን፤ ታላላቅ የዓለማችን መሪዎችና ታዋቂ ሰዎችም በማንዴላ ሞት ሀዘናቸውን እየገለፁ ነው።
በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን በስዌቶ በሚገኘው በቀድሞው የኔልሰን ማንዴላ መኖሪያ ቤት በመሰባሰብ በባህላዊ ስርአታቸው መሰረት በልዩ ልዩ የብሔረሰቦች የሀዘን ጭፈራ ለመሪያቸው ያላቸውን አክብሮች እየገለፁ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
የተለያዩ የዓለማችን መሪዎችና ታዋቂ ሰዎችም ለኔልሰን ማንዴላ አድናቆታቸውንና ሀዘናቸውን እየገለፁ ናቸው።
“ታላቅ ተጽዕኖ ፈጣሪና የተስፋ ሰው የነበሩት ማንዴላ በህይወታቸው በፈጸሟቸው ታላላቅ ተግባራት ምንጊዜም ስንዘክራቸው እንኖራለን”ያሉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ናቸው።
ተመሳሳይ አድናቆታቸውን እና ሀዘናቸውን ከገለፁ ሰዎች መካከል የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ ባን ኪ ሙን፣ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ-ቺንፒንግ፣ የፈረንሳዩ ፍራንኮይስ ሆላንዴ፣ የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርከል፣ የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፣ የኖቬል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ሉሬት ኢሌን ጆንስተን ሲርሊፍ የብራዚል ፕሬዚዳንት ዲልማ ሩሴፍ፣ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞሀል ሲንግ፣ የኢንግሊዟ ዳግማዊት ንግስት ኤልሳቤት ፤ የእንግሊዙ ጠ/ሚ/ር ዴቪድ ካሜሩን፣ የእስራኤል ጠ/ሚ/ር ቤንያሚን ኒያትኒያሁ፣ የፍልስጥኤሙ መሪ መሀሙድ አባስ፣የኢራን ፕሬዚዳንት ሀሰን ሩሀኒ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
በኔልሰን ማንዴላ ዜና እረፍት በእጅጉ ማዘናቸውን በርካታ ኢትዮጵያውያን ለኢሳት በመደወል ገልጸዋል። አንዳንዶቹ ከማንዴላ የተማርነው ይቅርባይነትን ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ጽናትንም ያክላሉ። ብዙዎቹ ወጣቶች፣ በጽናት መታገል ውጤታማ እንደሚያደርግ ከጀግናው መሪ ተምረናል ብለዋል። ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል የተወሰኑት የሚከተለውን ይመስላል።
የኔልሰን ማንዴላ የቀብር ሥነ-ስርዓት የሚፈፀመው እሁድ ዲሴምበር 15 ቀን እንደሆነ የወቅቱ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ አስታውቀዋል።