ህዳር ፲፪(አስራ ሁለት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢሳት በደረሰው አስተማማኝ መረጃ መሰረት በሳውድ አረቢያ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ለትምህርት ቤት መገንቢያ እና ለችግር ግዜ ይሆነናል በማለት ከግል ኪሳቸው እያወጡ በደረግ ዘመን ሲያጠራቅሙት የነበረውን ገንዘብ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በሰጡት ትእዛዝ ገንዘቡ ተወርሶ በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲና የአምባሳደሩ መኖሪያ እንዲሁም ጅዳ የሚገኘው የቆንስላ ጽህፈት ቤት እንዲሰራበት ተድርጓል።
ኮሚኒቲው በወቅቱ 50 ሚሊዮን ሪያል ወይም በጊዜው በነበረው ምንዛሬ ከ13.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ነበረው። የኮሚኒቲው መሪዎች ገንዘቡ እጅግ በጣም ከፍተኛ በመሆኑና ምናልባትም የሳውዲ መንግስት አይን ሊያርፍበት ይችላል በሚል ምክንያት በኢትዮጵያ ኢምባሲ አካውንት እንዲቀመጥላቸው እና ገንዘቡን ሲፈልጉ ከአምባሳደሩ ጋር በጋራ በመሆን እንዲያንቀሳቀሱ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ስምምነት በማድረጋቸው፣ ገንዘቡ በኢትዮጵያ ኢምባሲ አካውንት እንዲቀመጥ ተደርጓል። ገንዘቡም በኮሚኒቲው ሊቀመንበር እና ተቀማጭነቱ ጅዳ በነበረው ቆንሲላ ጄኔራሉ ፊርማ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።
ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ ገንዘቡን ለመጠቀም በመፈለጉ የኮሚኒቲ መሪዎችን በጥቅማጥቅም ለመደለል ዘመቻ ጀመረ። ለኮሚኒቲ መሪዎቹ አዲስ አበባ ውስጥ መሬት እንደሚሰጣቸውና ቤቶችን ሰርተው እንደሚኖሩ ፣ መንግስት መሪዎቹ ለሚያቀርቡት ጥያቄ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተነግሮአቸዋል። ይሁን እንጅ የስደተኞች ተወካዮች ገንዘቡ የህዝብ በመሆኑና ትምህርት ቤት ለመስሪያ እንዲሁም ለችግር ጊዜ የሚቀመጥ በመሆኑ፣ ገንዘቡን መንግስት እንዲጠቀምበት አንፈቅድም የሚል መልስ ሰጡ።
በጉዳዩ ላይ እጃቸውን ያስገቡት አቶ መለስ ለአንዳንድ የኮሚኒቲው መሪዎች ” መሬት እንኳ ባይኖር መስቀል አደባባይን ሸንሽኜ አከፋፍላችሁዋለሁ” በማለት ቃል እስከመግባት ደርሰው ነበር። የኮሚኒቲ መሪዎች የአቶ መለስን ማባበያ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸው ሲታወቅ አቶ መለስ ገንዘቡ ለግንባታዎች እንዲውል ቀጥተኛ ትእዛዝ ሰጡ።
በዚህ የተበሳጩት የወቅቱ የኮሚኒቲው መሪ አቶ እርቁ ገዳ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ቢፈልጉም፣ ኢምባሲው ግትር ናቸው የተባሉት ሊቀመንበሩ በሌላ የኢህአዴግ ደጋፊ እንዲተኩ በማስደረግ ክሱ እንዳይንቀሳቀስ አድርጓል።
አንዳንድ የኮሚኒቲው መሪዎችም ምንም ማድረግ አለመቻላቸውን ሲያዩ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ቃል የተገባላቸው ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ይሁን እንጅ የጠየቁትን ቦታ ካለማግኘታቸውም በላይ አንዳንዶች መንግስት በጠየቃችሁ ጊዜ ግትር አቋም አሳይታችሁዋል በሚል የተለያዩ ችግሮች እንዲደርስባቸው ሆኗል።
አንዳንድ ሰዎች ገንዘቡን የኢትዮጵያ መንግስት ባይጠቀምበት ኖሮ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ በሳውዲ አረቢያ የሚገኙና ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ሰዎችን ለመርዳት ሊውል ይችል እንደነበር አስተያየት ሰጥተዋል።
የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትን አስተያየት ለማግኘት በመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የእጅ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም፣ ስብሰባ ላይ ነኝ የሚል መልስ በመስጠታቸው ሊሳካልን አልቻለም።
ጉዳዩን በቅርቡ ከሚያውቁ ሰዎች ጠይቀን እንደተረዳነው በወቅቱ መንግስት የሳውዲ አረቢያን የኢትዮጵያ ኪሚኒቲ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም የገልፍ አገሮች የኮሚኒቲ ገንዘቦችን በመውሰድ ለግንባታው አውሎአል።
የሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ካቋቋሙዋቸው ኮሚኒቲዎች ሁሉ ጠንካራው ነው። ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ገንዘብ በመላክ ቅድሚያ ሲናራቸው በአደጋ ጊዜ በተለይም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁትን ሰዎች ያነጋገርን ሲሆን፣ ሁኔታዎች እንደፈቀዱ የምናቀርብ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።