ከሳውድ አረቢያ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያንን ቁጥር በተመለከተ የመንግስት ባለስልጣናት የሚሰጡት መግለጫ ህዝቡን ጥርጣሬ ላይ ጥሎታል

ህዳር ፲፪(አስ ሁለት )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ዘግይቶም ቢሆን ችግረኛ ኢትዮጵያውያንን ከሳውድ አረቢያ ማስወጣት የጀመረው የኢትዮጵያ መንግስት፣ እስካሁን ድረስ የተመላሾችን አሀዝ በተመለከተ የሚሰጠው መግለጫ ግን ህዝቡን ጥርጣሬ ላይ መጣሉን የኢትዮጵያው ዘጋቢያችን ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም በቲውተር ወደ አገር ቤት የተመለሱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 10 ሺ 707 ነው በማለት ገልጸዋል።

ይሁን እንጅ የእርሳቸው ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የተመላሹን ቁጥር በ6 ሺ በማሳነስ  4 ሺ 961 ሰዎች መግባታቸውን ለጀርመን ራዲዮ ተናግረዋል።  ሁለቱም ባለስልጣናት  መግለጫዎችን የሰጡት በአንድ ቀን ውስጥ ሲሆን አንዳንድ ወገኖች ይህን ያክል ቁጥር ያለው ልዩነት እንዴት ተፈጠረ ሲሉ ጠይቀዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ሁለቱንም ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።