የስዊድን የጦር ፍርድ-ቤት አቃቢ-ህግ በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ወሰነ፡፡

ህዳር ፲፩(አስ አንድ )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-የጦር ፍርድ ቤቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በቅርቡ በኦጋዴን የተፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመለከተ፣ የክልሉ የወጣቶች ሊቀመንበርና የፕሬዚዳንቱ የግል ዌብሳት ማኔጀር እና አማካሪ የነበረው ወጣት አብዱላሂ ሁሴን በኦጋዴን የጦር ወንጀልና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መፈጸሙን የሚያሳይ ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ አቃቢ ህግ ማቅረቡን ተከትሎ ነው።

የጦር ፍርድ ቤቱ ዋና አቃቢ ህግ ክሪስተር ፒተርሰን በ10 የኦጋዴን ክልል ባለስልጣናትና የመከላከያ አዛዦች ላይ የቅድመ መርምራ እንዲካሄድ የወሰኑ ሲሆን ከተመርማሪዎች መካከል የክልሉ ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሀመድ ኡመርና ምክትሉ አብዱላሂ ዌረር እንደሚገኙበት ወጣት አብዱላሂ ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ገልጿል።

ውሳኔው ለኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ድል ነው ያለው አብዱላሂ፣ ምርመራ መጀመሩንም ገልጿል።

ምርመራው እንደተጠናቀቀ ሁለት አማራጮች ሊኖሩ እንደሚችል ተናግሯል። አንደኛው አማራጭ ጉዳዩን በስዊድን የጦር ፍርድ ቤት ማየት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ወደ አለማቀፉ የወንጀል ፍርድቤት መላክ ነው።

በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መረጃዎችን በመላክ እንዲሁም የምስክርነት ቃላቸውን በመስጠት እንዲተባበሩ ወጣት አብዲ ገልጿል።

በሌላ በኩል በተለያዩ የአለም ክፍሎች  የሚገኙና በኢትዮጵያ መንግስት በደል  የደረሰባቸው ሰዎች መረጃዎቻቸውን እንዲሁም የምስክርነት ቃል ለመስጠት የሚፈልጉ የስልክ ቁጥራቸውን በ0031 68 71 54 530 ወይም በ [email protected] ቢልኩ  ኢሳት ጉዳዩን በቅርብ ከሚከታተሉ ወገኖች ጋር የሚያገናኛቸው መሆኑን ለመግልጽ ይወዳል።