ጥቅምት ፳(ሃያ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የጥሬ ቆዳና ሌጦ ኤክስፖርት ባለፉት አምስት ዓመታት የተሻለ ገቢ ያስገኘ ቢሆንም ግብይቱ ኃላቀር፣ሰንሰለቱ የተንዛዛና ከፍተኛ የግብይት ወጪዎች የሚታዩበት እንዲሁም በምርት ጥራት በኣለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቱ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ አመለከተ፡፡
የጥሬ ቆዳና ሌጦ ኤክስፖርትን በማቆም እሴት የተጨመረባቸውን የተለያዩ የቆዳ ውጤቶች ለውጪ ገበያ በመላክ የተሻለ የውጪ ምንዛሪ ለማስገኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን መረጃው ጠቁሞ ዘርፉን ከብክነትና ከጥራት ጉድለት ግን መታደግ ባለመቻሉ አሁንም በብዙ ችግሮች ውስጥ የሚውተረተር ሆናል ይላል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት ከዘርፉ 430 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን ጠቁሞ ይህ ግን ዘርፉ ማመንጨት ካለበት ገቢ ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ገቢ ነው፡፡
የእንስሳት እርባታው ከውልደት ጀምሮ ኃላቀርና በባህላዊ ዘዴ በመከተል የሚከናወን በመሆኑ የቆዳና ሌጦ ጥራቱ ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን፣በእርድ ወቅትና ከእርድ በኃላ የሚከሰቱ የተለያዩ የጥራት ጉድለቶች መኖራቸው ፣የግብይት
ሒደቱ ኃላቀር ፣የተንዛዛ፣ ቅብብሎሽ የበዛበትና እሴት የማይጨምሩ ግን ዋጋ የሚያንሩ ተዋንያን የበዙበት መሆኑ እንዲሁም ለንዑስ ዘርፉ ልማት እና ግብይት ጠንካራ አደረጃጀት አለመፈጠሩ እንደችግር ተጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል የጥራት ችግር እያመጣ ባለው የውጪ ጥገኛ በሽታ አምጪ ህዋሳት ላይ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በሽታዎቹ በሚያይሉባቸው በሰሜኑ የኢትዮጽያ ክፍል ማለትም በአማራ፣በትግራይና በአፋር ክልሎች የኬሚካል ርጭት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ መሆኑን መረጃው ይጠቁማል፡፡ ይህም ሆኖ የኬሚካል ርጭቱ በአማራ ክልል መጠነኛ ለውጥ ያሳየ ቢሆንም በሌሎቹ ክልሎች ውጤቱ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በዚህ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ተጨማሪ 25 ሚሊየን ብር በጀት ተይዞ በመላ አገሪቱ የኬሚካል ርጭቱ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሷል፡፡