ጥቅምት ፲፪(አስራ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ክልተ አውላዕሎ ወረዳ ፣ አይናለም እየተባለ በሚጠራው ጣቢያ በቤተክርስትያን ግንባታ ምክንያት በህዝብና አስተዳዳሪዎች መካከል አምባጓሮ ተፈጥሮ አንድ ቄስ ተገድለዋል። የመቀሌው አብርሀ ደስታ እንደዘገበው ፣ ቄሱ ህዝብና ቤተክርስትያኑ ወክለው ከመንግስት አካላት ጋር ሲከራከሩ የነበሩ ሲሆን በመንግስት ካድሬዎች የተለያየ ዛቻ ሲደርሳቸው ቆይቶ ማንነቱ ባልታወቀ ሰው በሌሊት ተገድለው ተገኝተዋል። ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም አያይዞ ዘግባል።
መንግስት ቤተክርስትያኑ እንዳይገነባ ያዘዘው ቤተክርስትያኑ ያረፈበት ቦታ አንድ የህወሓት ደጋፊ ባለሃብት ለኢንቨስትመንት ስለመረጠው ተብሎአል።
በተምቤን ጣንቋ አበርገለ ወረዳ የመንግስት ካድሬዎች በቤተክርስትያን የፖለቲካ ስብሰባ እየጠሩ ምእመናንን ስላስቸገሩ አንድ የቤተክርስትያኒቱ ቄስ በቤተክርስትያን የፖለቲካ ስብሰባ እንደማይፈቀድ ለካድሬዎቹ በመናገራቸው ቄሱ ለቀናት ታስረው መለቀቃቸውንም አብርሀ ዘግቧል።
ቄሱ ” በቤተክርስትያን የፖለቲካ ስብሰባ እንደማይፈቀድ ማወጃቸውን ተከትሎ ካድሬዎም “ፀረ ዉድብና” በሚል ሰበብ እንዳሰሩዋቸው ተገልጻል።
ዜናውን ለማጣራት ለክልሉ ፖሊስ በተደጋጋሚ ብንደውልም አልተሳካልንም።