የአቶ አስገደ ገብረስላሴ ልጆች በከፍተኛ ስቃይ ላይ ናቸው

ጥቅምት ፲፪(አስራ ሁለት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ነባር የህወሀት ተጋይ የነበሩትና በአሁኑ ጊዜ በገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው የሚገኙት ታዋቂው ታጋይ አቶ አስገደ ገብረስላሴ ፣ ልጆቻቸው በከፍተኛ ስቃይ ላይ እንደሚገኙ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

የማነ  የተባለው ልጃቸው፣ በእስር ቤት ላይ በደረሰበት ግፍ ምክንያት አካል ጉዳተኛ ሆኗል። አህፎም ደግሞ ከስራ ገበታው ላይ ታፍኖ ከተወሰደ በሁዋላ፣ ላለፉት 7 ወራት ያለምንም ፍትህ በእስር ላይ ይገኛል።

አክብሮም የተባለው የ10 ኛ ክፍል ተማሪ ኳስ እየተጫወተ ባለበት ጊዜ በፖሊሶች ተወስዶ ታስሯል። ከስድስት ቀናት በሁዋላ ለሚመለከታቸው አካላት ካቀረቡ በሁዋላ እስር ቤት ሄደው ለማየት መቻላቸውን ገልጸዋል።

አቶ አስገደ፣ ህወሀት በእርሳቸው ላይ በትሩን ካሳረፈ በሁዋላ አሁን ደግሞ ወደ ልጆቻቸው ማዞሩን ተናግረዋል ። በልጆቼ ላይ የሚደርሰው በሌሎች ልጆች ላይ ሁሉ የሚደርስ በመሆኑ ሁሉም ዜና ሊረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ትግራይ ጭንቅ ውስጥ ናት ያሉት አቶ አስገደ፣ ክልሉ ጨለማ ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል። ስደት፣ ስራ አጥነት፣ የፍትህ እጦት እና ሙስና በክልሉ መስፋፋቱን ገልጸዋል።

የአቶ አስገደን  ሙሉ ቃለ ምልልስ ሰሞኑን ይቀርባል።