ጥቅምት ፲(አስር)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስት ራሱ የ 40 በ 60 መኖሪያ ቤት ሠርቶ ለመስጠት የሰጠውን መግለጫ አምነው ከ81 ሺህ ሰዎች በላይ ሙሉ ክፍያ ከፈፀሙ በሁዋላ፤ ሀሳቡን በመቀየር ከፋዮቹ በማህበር ተደራጅተው ቤቱን ራሳቸው እንዲሠሩ መወሰኑ ተመዝጋቢዎችን አሳዝኗል።
እንደ ሪፖርተር ዘገባ በአሁኑ ጊዜ መቶ በመቶ የከፈሉ የ40/60 ተመዝጋቢዎች በመኖርያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር ወደ ተነደፈው ፕሮግራም እንዲዛወሩ የአዲስ አበባ አስተዳደር ማግባባት ጀምሯል፡፡
ሆኖም ክፍያ የፈፀሙ ዜጎች በመኖርያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፕሮግራም ተደራጅተው ቤቶችን ሲገነቡ፤ ህጉ ከይዞታቸው ለሚፈናቀሉ ሰዎች ራሳቸው ካሳ እንዲከፍሉ ስለሚያስገድዳቸው አዲሱ የመንግስት ሀሳብ ብዙዎችን ስጋት ላይ ጥሏቸዋል።
መንግስት ክፍያ የፈፀሙት በማህበር እንዲደራጁ ለጀመረው ማግባባት እስካሁን ምላሽ ያገኘው ከ አንድ በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆነም ተገልጿል።
አንድ የከተማው አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ ከ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ውስጥ መቶ በመቶ የከፈሉት ወደ ማኅበራት እንዲዛወሩ የተፈለገው እነዚህ ወገኖች መቶ በመቶ የመክፈል አቅም ካላቸው፣ የራሳቸውን ቤት ራሳቸው እንዲገነቡና መንግሥት ላይ ያለው ጫና እንዲቀንስ በሚል ሐሳብ ነው ብለዋል።
በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም 81,257 ነዋሪዎች መመዝገባቸው ይታወቃል፡፡
በሦስቱም የመኖርያ ቤቶች ማለትም በ 40//60 ፣በ10/90 እና በ20/80) ፕሮግራሞች የተመዘገቡ ነዋሪዎች 2.5 ቢሊዮን ብር እንደቆጠቡ ፤ይሁንና የእነዚህን ቤቶች ግንባታ ለማስጀመር መንግሥት ተጨማሪ 7.5 ቢሊዮን ብር እንደመደበ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሐሙስ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልፀው ነበር።
ዜጎች የመንግስትን ቃል አምነው ክፍያ ከፈፀሙ በሁዋላ መንግስት ሀሳቡንና አሠራሩን መቀየሩ ከህግ አኳያ ውል እንደማፍረስ ነው ያሉ አንድ የህግ ባለሙያ፤ ሁኔታው ከዚህም ባሻገር ፕሮግራሙ ሲጀመር፦”መንግስትን አምናችሁ እንዴት ገንዘባችሁን ቀድማችሁ ትከፍላላችሁ እያሉ ሲመክሩ የነበሩ ዜጎችን ስጋት ተገቢነት” ያመላከተ ነው”ብለዋል።