መለስ የሚባል ራእይ የለም ሲሉ አቶ ስብሀት ነጋ ተናገሩ

ጥቅምት (አስር)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ(ህወሀት) ውስጥ የተካረረ አለመግባባት እንደተፈጠረ በስፋት በሚነገርበት በዚህ ወቅት አቶ ስብሀት ነጋ ፣ የኢህአዴግ እንጂ የመለስ የሚባል ራእይ የለም ብለዋል።

የህወሀት መስራች የሆኑት አቶ ስብሀት ነጋ ይህን ያሉት ከጋዜጠኛ ደረጀ ደስታ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው።

አቶ ስብሀት ፦” መለስ የ ኢህአዴግን ራዕይ ለማስፈፀም ከፊት ሆኖ ብዙ ሥራ ሠራ እንጂ ራዕዩ የመለስ አይደለም። ራይዩ የድርጅቱ ነው”ብለዋል።

በዚሁ ቃለ-ምልልስ ከሟች ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት ከወይዘሮ አዘዜብ መስፍን ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብተው እንደነበርም አቶ ስብሀት በግልጽ ተናግረዋል።

አቶ ስብሀት በዚሁ አስገራሚ መልሶችን በሰጡበት ቃለ-ምልልስ የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ ስለተሾሙት  33 ጀነራሎች ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለም ተናግረዋል።

አቶ መለስ ማረፋቸውን ተከትሎ ከ አራቱ የ ኢህአዴግ ድርጅቶች በተውጣጡ  አራት ምክትል ጠ/ሚ/ሮች  እየተመራች ያለችው ኢትዮጵያ፤ያም አልበቃ ብሎ  ከአራቱም ድርጅቶች የተውጣጡ አራት ከፍተኛ ካድሬዎች  አማካሪዎች ተብለው አቶ ሀይለማርያም አጠገብ እንዲሆኑ መደረጋቸው ይታወሳል።

አቶ ሀ ይለማርያም ደሳለኝም አመራራቸውን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ፦በጋራ፣በኮሚቴ እየመራን ነው ማለታቸው አይዘነጋም።