የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ ከፍተኛ ድክመት እየታየበት ነው

ጥቅምት (አስር)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-የንግድ ሚኒስቴርና የክልሉ ቢሮዎች የ2006 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ  በጊዎን ሆቴል ባደረጉበት ወቅት ሚኒስቴሩ አቶ ከበደ ጫኔ ” በ2005 የበጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም የታሰበውን ያክል ትርፋማ መሆን አልተቻለም፡፡” ብለዋል።  ችግሮቹ ሐገራዊ ፣ አለማቀፋዊና አህጉራዊ ይዘት እንዳላቸውም ሚኒስትሩ አክለዋል።

በ2005 በጀት አመት 4 ቢሊዮን 600 ሚሊዮን  ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዶ  68 ነጥብ ስድሰት ከመቶውን ብቻ በመሳካቱ የታሰበውን ያክል ትርፋማ ለመሆን አለመቻሉንና  በንግድ ትስስሩም ደካማ ውጤት መመዝገቡን ገልጸወዋል።

በ2003 በጀት ዓመት የንግድ ሚኒስቴር ስኳር ወደ ውጭ  በመላክ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢያቅድም ፣ የሀገር ውስጥ ፍጆታን እንኳን መሸፈን ባለመቻሉ እቅዱ አልተሳካም፡፡  ወደ ውጭ የተላከው ቡና መጠን ቢጨምርም ዋጋው  ግማሽ ያህል መቀነሱም ተመልክቷል፡፡ የሰሊጥ ዝንጅበልና ጥራጥሬ ዋጋ በአጠቃላይ ሲታይ ከፍተኛ ቢሆንም  ምርቱ ቅናሽ አሳይቷል ፡፡ የቆዳና ጨርቃጨርቅ ምርት ወደውጭ በመላክ  ጠቀም ያለ ምንዛሬ ለማግኘት ጉጉት ቢኖርም የፋብሪካዎች ግንባታ መጓተት እቅዱ እንዳይሳካ አድርጎታል፡፡

አቶ ዙስማን አህመድ፣  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ የግባዓት ግብይት ምክትል ቢሮ ሀላፊ ‹‹የ2005 በጀት ዓመት አፈፃፀም ከስኬት መስመር እንዲያፈነግጥ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል በክልሎችና በንግድ ሚኒሰቴር መካከል ወጥ የሆነ የግብይት ስርዓት ያለመኖሩ ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል ግብዓትና ህብረት ስራ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ  አቶ በላይ ባራሞ ደግሞ እንደ ቡና ፣ ቦለቄና ሌሎች ገበያ ተኮር ምርቶች ዋጋ ወጥነት ማጣት አምራቾች ወደ ጫት ምርትነት እንዲገቡ እያደረጋቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡