ጥቅምት ፲(አስር)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ(ህወሀት) ውስጥ የተካረረ አለመግባባት እንደተፈጠረ በስፋት በሚነገርበት በዚህ ወቅት አቶ ስብሀት ነጋ ፣ የኢህአዴግ እንጂ የመለስ የሚባል ራእይ የለም ብለዋል።
የህወሀት መስራች የሆኑት አቶ ስብሀት ነጋ ይህን ያሉት ከጋዜጠኛ ደረጀ ደስታ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው።
አቶ ስብሀት ፦” መለስ የ ኢህአዴግን ራዕይ ለማስፈፀም ከፊት ሆኖ ብዙ ሥራ ሠራ እንጂ ራዕዩ የመለስ አይደለም። ራይዩ የድርጅቱ ነው”ብለዋል።
በዚሁ ቃለ-ምልልስ ከሟች ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት ከወይዘሮ አዘዜብ መስፍን ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብተው እንደነበርም አቶ ስብሀት በግልጽ ተናግረዋል።
አቶ ስብሀት በዚሁ አስገራሚ መልሶችን በሰጡበት ቃለ-ምልልስ የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ ስለተሾሙት 33 ጀነራሎች ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለም ተናግረዋል።
አቶ መለስ ማረፋቸውን ተከትሎ ከ አራቱ የ ኢህአዴግ ድርጅቶች በተውጣጡ አራት ምክትል ጠ/ሚ/ሮች እየተመራች ያለችው ኢትዮጵያ፤ያም አልበቃ ብሎ ከአራቱም ድርጅቶች የተውጣጡ አራት ከፍተኛ ካድሬዎች አማካሪዎች ተብለው አቶ ሀይለማርያም አጠገብ እንዲሆኑ መደረጋቸው ይታወሳል።
አቶ ሀ ይለማርያም ደሳለኝም አመራራቸውን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ፦በጋራ፣በኮሚቴ እየመራን ነው ማለታቸው አይዘነጋም።