ጥቅምት ፰(ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም
ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የፓለቲካ እስረኞች ላይ ምርመራ ሲያካሂዱ ስቃይ እንደሚፈጽሙ ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው ሂዩማን ራይትስ ዎች ዛሬ ይፋ አደረገ፡፡
መንግስት በበኩሉ የቀረበውን ውንጀላ አስተባብሎ ሪፖርቱ ከእውነት የራቀና ተአማኝነት የሌለው ነው ብሏል፡፡
ድርጅቱ ታስረው የነበሩ እማኞች ዋቢ በማድረግ ባወጣው ሪፖርት ባለስልጣናት ከእስረኞች ቃል ለመቀበል ሲሉና ምርመራ ሲያካሂዱ ድብደባ እንደሚፈጽሙ አመልክቷል፡፡
በተለይ የጸጥታ አካላትና ፓሊሶች በማዕከላዊ እስር ቤት ህገ ወጥ የሆነ የምርመራ አካሄድ እንደሚጠቀሙ እና እስረኞችን ተገቢ ባልሆነ አያያዝ በማቆየት ከጠበቃ ጋር እንደማያገኟቸው ተገልጿል፡፡
የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ለሲሊ ሌፍኮው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የፖለቲካ ፓርቲ አባላትንና ጋዜጠኞችን በመደብደብና በማሰቃየት መረጃዎችን እንዲያወጡ ያስገድዳሉ ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል ሪፓርቱ ማረጋገጫ የሌለውና 35 የቀድሞ ታሳሪዎችን ብቻ ዋቢ ያደረገ ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
በሪፖርቱ ከሁለት ዓመት በፊት በኦጋዴን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ከተያዙትና 400 ቀናትን በእስር ካሳለፉት ሁለት የሲውዲን ጋዜጠኞች የአንደኛው እማኝነት ተካቶበታል፡፡
ሁለቱ ጋዜጠኞች በይቅርታ ከተፈቱ በኋላ የኢትዮጵያ የፀጥታ አካላት መሳሪያ ደግነውባቸው የውሸት ቃል እንዲሰጡ መገደዳቸውን በተደጋጋሚ ሲያሳውቁ ቆይተዋል፡፡
‹ማሰቃየትና ጎጂ አያያዝ በኢትዮጵያ ፖሊስ ጣቢያ በሚል ርዕስ ይፋ የሆነው ባለ 74 ገጽ ሪፖርት በእስር ላይ ቆይተው የነበሩ 35 ታሳሪዎችን በእማኝነት ያካተተ ሲሆን በቅርቡ የጸደቀው የፀረ ሽብርተኛ ህግ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ እስረኞችን ለማፈን እየዋለ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
አንድ የኦሮሞ ተማሪ እስር ቤት በነበረበት ወቅት እጆቹ እንደታሰሩ ምግብ እንዲበላ ሲደረግ እንደነበር እማኝነቱን ሰጥቷል፡፡
ተማሪው ምግብ በሚበላ ሰዓት ወደ ኋላ ታስረው የነበሩ እጆቹ ወደ ፊት ተደርገው በመታሰር ምግብ እንዲበላ ተደርጎ ከበላ በኋላ ግን ተመልሶ እጆቹ ወደ ኋላ እንደሚታሰሩ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አባላት ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ሶስት ጊዜ ማዕከላዊ እስር ቤትን ቢጎበኙም የእስር ቤቱ ሀላፊዎች አብረው በመሆን እስረኞቹ ከአባላቱ ጋር በግል ጉዳያቸውን እንዳይናገሩ ያደርጋሉ ሲል ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ማዕከላዊ በመባል የሚታወቀው የፌደራል ወንጀል ምርመራ ውስጥ የሚፈፀመው ህገ ወጥ ተግባራት ለማስቆም እንዲሁም የሚፈጸሙትን በደሎች በተመለከተ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ እና አጥፊዎቹንም ተጠያቂ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ድርጅቱ ጠይቋል፡፡