የዋግ ህምራ ህዝብ ከመንገድ ጋር በተያያዘ ጩኸት ማሰማቱን ቀጥሎአል

ጥቅምት (ስምንት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ከመንገድ ጋር በተያያዘ ከዋግ ህምራ ዞን ርዕሰ ከተማ ሰቆጣ የሚሰማው የተቃውሞ ድምጽ በሁሉም የዞኑ ወርዳዎች መዳረሱን በስፍራው ያሉ ወኪሎች ገልጸዋል፡፡ ” የልማት ጥያቄያችን አልተመለሰም ፤  መንግስት ሰቆጣን እረሰቱዋል ፤ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ትግራይ መሄድ ግድ ብሎናል” ሲሉ ነዋሪዎች ለመንግስት ባለስልጣናት  ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በቅርቡ ከሰቆጣ ፤ አበርገሌ ፤ ዝቋላ፤ ስሃላ ሰየምት ፤ድሃና ፤ ጋዝ ጊብላ ፤ አበርገሌ እና ሌሎችም ወረዳዎች የተወጣጡ ቁጥራቸው ከ 30 ሺ በላይ የሆነ ህዝብ በከተማው አደባባይ በመውጣት ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡  “በሞትን ፤ በቆሰልን እና በደማንላት አገር ተረስተን ወድቀናል  በማለት ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በምስራቅ ና በሰሜን ከትግራይ፤ በደቡብ ከሰሜን ወሎ ፤ በምዕራብ ከሰሜን ጎንደር የሚዋሰነው የዋግ ህምራ ዞን ከኮረም ሰቆጣ ፤ ከዓለም ከተማ በላሊበላ በኩል እስከ አክሱም እና መቀሌ የተዘረጋውን የትግራይ ወረዳዎችን እስኪያገኝ ድረስ እስከ ሞት የሚደረስ አደጋ ያጋጥመዋል።( 09፡23-11፡48)

በዞኑ ምርታማ ነው ተብሎ ከሚታሰበው 168 ሺ 632 ሰው ውስጥ 124 ሺ 345 የሚሆነው ቤተሰብ የምግብ ዋስትናው አልተረጋገጠም፡፡ 148 ሺ የሚሆነው የዞኑ ኗዋሪ በማህበረሰብ ሴፍትኔት ፕሮግራም ተረጅ ነው፡፡  መንገድ መርቶ ያሳየ የዋግ ህዝብ መንገድ ተነፍጎታል በማለት የሚናገሩት ነዋሪዎች ፣ አሁንም በአፋጣኝ መንገድ እንዲሰራላቸው ጠይቀዋል።

ከተቃውሞ ሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አንዱን አነጋግረን እንደገለጹት፣ ከተቃውሞው በሁዋላ መንግስት መንገዱን ከ5 እስከ7 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚያስጀምር ቃል መግባቱን ገልጸዋል።

የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች በከተማዋ የተካሄደውን ስብሰባ ቀረፀው በመላካቸው ለማመስገን እንወዳለን።