ጥቅምት ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል በጋሞጎፋ ዞን በጨንጫ ወረዳ የሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤት መምህራን ለአባይ ግድብ ማሰሪያ በሚል ከደሞዛቸው ላይ ገንዘብ መቆረጡን ተከትሎ ካለፉት 3 ቀናት ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ እያደረጉ ነው፡፡
የጨንጫ ፣ ጭነቶ፣ ጦሎላ፣ ጨፌ፣ ጺዳ እና ቱክሻ ትምህርት ቤቶች መምህራን በአድማ ላይ መሆናቸውን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ተማሪዎች ቤታቸው ለመቀመጥ ተገደዋል።
የወረዳው እና የዞን መምህራን ማህበር ከመምህራኑ ጋር በመሆን አድማውን እያስተባበሩ ሲሆን፣ አድማው ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች እና አካባቢዎች ሊዛመት እንደሚችል መምህራን ለኢሳት ገልጸዋል።
መምህራን ” ደሞዛችን በግድ መቆረጡ አንሶ፣ እኛ በጠየቅነው ቀርቶ ባልጠየቅነው ወር ለምን ይቆረጥብናል ” በማለት አድማውን እንደ ጀመሩ አንድ መምህር ገልጸዋል ።
መምህራን የአንድ አመት ደሞዛቸውን ካስቆረጡ በሁዋላ፣ ከመስከረም ጀምሮ ደግሞ ሁለተኛውን ዙር ማስቆረጥ ጀምረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት መምህራን ለአባይ ግድብ ማሰሪያ በፈቃዳቸው ከደሞዛቸው እንዳስቆረጡ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።