በዳውሮ ዞን አዲስ ውጥረት ተቀሰቀሰ

ጥቅምት ፰(ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል ዳውሮ ዞን ከሁለት ዓመት በፊት ተቀስቅሶ የነበረው የመልካም አስተዳደር እጦት ጥያቄ በአዲስ መልክ መቅረብ በመጀመሩ በዞኑ ውጥረት መንገሱን ተገለጸ፡፡

በዞኑ የሚኖሩ ማህበረሰብ ከፍተኛ የሆን የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለባቸው በመግለጽ ላይ መሆናቸውን የዳውሮ ዞን አካባቢ ተወላጅ የሆኑት አቶ ፍሰሀ ተስፋዬ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አመልክተዋል፡፡

አዲስ መነሳት የጀመረውን የህዝብ ጥያቄ ተከትሎም ቁጥር ወደ 300 የሚጠጋ ልዩ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና አድማ በታኝ በዞኑ መስፈራቸው ታውቋል፡፡

የሰራዊቱን በቦታው መሰማራት ተከትሎ በርካታ ሰዎች ወደ አጎራባች ዞኖች ቀበሌዎች መሰደዳቸውን  አቶ ፍሰሀ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዞኑ የሚገኙ 20 ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን ህዝቡ ከመንግስት ተወካዮች ጋር ጥያቄያቸው መፍትሔ ካላገኘ ለመነጋገር እንደማይፈልጉ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

አዲስ በተቀሰቀሰው የህዝብ ቁጣና ብሶት የዞኑ አስተዳዳሪ በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን እንደለቀቁ አቶ ፍሰሀ ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ተሰማርተው የሚገኙ የሰራዊት አባላት በአንድ ክሊኒክ ውስጥ ሰፍረው ይገኛሉ የሚሉት የአካባቢው ተወላጅ ውጥረቱ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይቀየር ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የዋካን ከተማ ወደ ዞንነት እንድትቀየር በተነሳ ጥያቄ በዞኑ በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው፡፡ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር እጦት ያስቆጣው የአካባቢው ነዋሪ የነበረው መምህር የኔሰው ገብሬ እራሱን አቃጥሎ መግደሉ ይታወሳል፡፡