ጥቅምት ፬(አራት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሕአዴግ ካድሬዎችን ለማሰልጠን የተገነባውን የፖለቲካ ማሠልጠኛ ተቋም በሚኒስትር ማዕረግ ሲመሩ የነበሩት አቶ አዲሱ ለገሰ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የተውጣጡ ምክትሎች ተሹመውላቸዋል፡ ፡ ከብአዴን አቶ ለገሰ ቱሉ፣ ከደሕዴን አቶ ወንድሙ ገዛኸኝ፣ ከሕወሓት አቶ ነጋ በርሄ ሲሆኑ፣ ከኦሕዴድ የተወከለው አመራር እስካሁን አለመታወቁን ሪፖርተር ዘግቧል።
ማሠልጠኛ ማዕከሉ በስድስት ዙሮች በርካታ ካድሬዎችን ያሰለጠነ መሆኑን የዘገበው ጋዜጣው፣ ካድሬዎቹም ከሥልጠና በኋላ በመንግሥትና በፓርቲ መዋቅሮች ውስጥ በተለያዩ የአመራር ደረጃዎች ላይ ተመድበዋል።
ሥልጠና ማዕከሉ ከሚያተኩርባቸው የሥልጠና ዘርፎች መካከል የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ የኢትዮጵያ ህዳሴና የኢሕአዴግ ታሪክ ይገኙበታል።
ኢሕአዴግ በ2007 ዓ.ም ለሚካሄደው ምርጫና መንግሥት የጀመራቸውን የልማት ሥራዎች እንዲሁም መልካም አስተዳደርን የሚያሰፍኑና ሙስናን የሚዋጉ አመራሮችን ለማፍራት ዕቅድ በአቶ አዲሱ ለገሰ የሚመራው የኢሕአዴግ ማሠልጠኛ ተቋም ከፍተኛ እምነት እንደተጣለበት ጋዜጣው ዘግቧል።
ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት የካድሬዎች ሥልጠናን አጠናክሮ ለመቀጠል የማሠልጠኛ ማዕከል እየገነባ ሲሆን ከዚህ የሥልጠና ማዕከል በተጨማሪ አራት ኪሎ አካባቢ ለሚገነባው የኢሕአዴግ ዋና የፖለቲካ ማዘዣ ጣቢያ ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ዝግጅት ማድረጉን ጋዜጣው ዘግቧል።
ከሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የተውጣጡ ምክትሎች እንዲሾሙ የተደረገበትን ምክንያት ጋዜጣው አላብራራም።
ኢህአዴግ ሰሞኑን እያካሄደው ባለው ግምገማ ከ5 ሚሊዮን አባላት ውስጥ 2 ሚሊዮኑ ብቻ እንደሚንቀሳቀሱ ፤ድርጅቱን የሚለቁ አባላት ቁጥራቸው እየተበራከተ መምጣቱንም መግለጹ መዘገቡ ይታወሳል።