ጥቅምት ፩(አንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዓለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፍትሀዊ ባልሆነ መልኩ በ አፍሪካ ላይ ስጋት እያሳደረ ነው ሲሉ አንድ ከፍተኛ የህብረቱ ባለስልየጣን መናገራቸውን ቢቢሲ ዘገበ።
የኢትዮጵያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሀኖም ይህን ያሉት፤ዛሬ በአዲስ አበባ በተጀመረው የህብረቱ ልዩ ስብሰባ ላይ ነው።
ቴዎድሮስ በስብሰባው ላይ ፦”ፍርድ ቤቱ ያነጣጠረው አፍሪካ ላይ ነው።”ማለታቸውን የገለጸው ቢቢሲ፤ በስብሰባው አፍሪካ ከዓለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንድትወጣ ግፊት እየተደረገ መሆኑን ጠቁሟል።
ህብረቱ ይህን የሁለት ቀናት አስቸኳይ ስብሰባ የጠራው፤’የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ክስ በሚቀጥለው ወር ዘሄግ በሚገኘው ፍርድ ቤት መታየት እንደሚጀምር በመገለጹ ነው።
.በኬንያ የተካሄደውን የ 2007 ምርጫ ተከትሎ ለተፈጠረው እልቅት ተጠያቂ የሆት ኡሁሩ ኬንያታ፤ ክሱ እንደማይመለከታቸው በተደጋጋሚ አስተባብለዋል።
ፕሬዚዳንት ኬንያታ ትናንት ሐሙስም ክሳቸው እንዲቋረጥ ጥያቄ አቅርበዋል። ይሁንና ስለ ንጽህናቸው በቪዲዮ ያቀረቡለትን ማስረጃ ያላመነበት ዓለማቀፉ ፍርድ ቤት፤ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ የ ኢትዮጵያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ከሌሎች የተወሰኑ የ አፍሪካ መሪዎች ጋር በመሆን “ያገለገሉ መሪዎችና ፓሬዚዳንቶች ለፍርድ ሊቀርቡ አይገባም” የሚል ግፊት እያደረጉ ነው።
የህብረቱ ሥራ አስፈጻሚ ካውንስል የወቅቱ ሊቀ መንበር ቴዎድሮስ በዚሁ ስብሰባ ላይ “ዓለማቀፉ ፍርድ ቤት በአፍሪካ ላይ የበላይነቱን እያሳየ ነው” ማለታቸውንም የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
“ፍርድ ቤቱ ፍትህንና እርቅን ከማወጅ ርቋል፤ አፍሪካን ማዕከል ባደረገ መልኩ ራሱን ወደ ፖለቲካ መሳሪያነት ቀይሯል፤ይህ ፍትሀዊ ያልሆነና የተሳሳተ አሠራር ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል ቴዎድሮስ።
በዚሁ ስብሰባ ላይ የኬንያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ፤ቀደም ሲል የተሰራጨውንና- የዓለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባል የሆኑ የአፍሪካ አገራት ከአባልነት እንዲለቁ ግፊት እየተደረገ ነው የሚለውን ዘገባ አስተባብለዋል።
ይህን በኢትዮጵያና በተወሰኑ አገሮች የተጀመረው በፍርድ ቤቱ ላይ ተቃውሞ የመጀመር እንቅስቃሴ በምስራቅ አፍሪካ መሪዎች ዘንድ እንደ በጎ የታየ ቢሆንም ፤ምዕራብ አፍሪካውያኑ ግን አልደገፉትም።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ቦትስዋና በግልጽ ፍርድ ቤቱን እንደምትደግፍ አሳውቃለች።
ይሁንና የዓለማቀፉ ፍርድ ቤት አባላት ከሆኑት 54 የ አፍሪካ አገሮች መካከል 34 ቱ ከ አባልነት ለመውጣት ፈርመዋል።
በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ከ አባልነት ለመውጣት መፈረማቸውን- የቀድሞው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ ኮፊ አናን የሀፍረት ምልክት ሲሉት፤ ደቡብ አፍሪካዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዴዝሞን ቱቱ በበኩላቸው ፦” በፍርድ ቤቱ ላይ ተቃውሞ እያሰሙ ያሉት የአፍሪካ መሪዎች ፤እንደገና ለመግደል.ለመጨፍጨፍና ለማረድ ፈቃድ የሚጠይቁ ይመስላሉ”ብለዋል።
ኢሳት ከሦስት ቀናት በፊት ባጠናቀረው ዘገባ፦ ” አፍሪካ ህብረት በአዲስ አበባ አስቸኳይ ስብሰባ እንደጠራ፤የስብሰባው ዋነኛ አጀንዳ በዓለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ ግፊት ማድረግ እንደሆነ እና ይህንንም በዋነኝነት እያስተባበረች ያለችው ኢትዮጵያ እንደሆነች መግለጹ ይታወሳል።