ሸህ መሀመድ ሁሴን አል ዓሙዲ ቤቶችን ተነጠቁ

ጥቅምት (አንድ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ከመንግስት ጋር ባላቸው ከመጠን ያለፈ ወዳጅነትና ቅርበት የሚታወቁት ሼህ መሀመድ ሁሴን አል-አሙዲ ለእግዶች ማረፊያ የተከራዩዋቸውን  ቤቶች እንደተነጠቁ የኢሳት ምንጮች ገለጹ።

ሼሁ፤ ከውጪ አገራት ለሚመጡባቸው እንግዶች በአያት ሲ.ኤም. ሲ   25 መኖሪያ ቤቶችን ለውጪ አገር ጎብኝዎች በተሰላ ሂሳብ ተከራይተው +በዶላር ምንዛሬ እየከፈሉ ሲገለገሉባቸው መቆየታቸውን የጠቀሱት እነዚሁ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ  ምንጮች፤ መንግስት ባልተገለጸ ምክንያትና የኪራይ ውሉን በማፍረስ  25ቱንም   ቤቶች ሰሞኑን እንደነጠቃቸው አመልክተዋል።

ባለሀብቱ አገር ውስጥ በሌሉበትና ባላወቁበት ሁኔታ የተወሰደው እርምጃ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ የሚድሮክ ሠራተኞችንና የባለሀብቱን ወዳጆች ማስደንገጡ ታውቋል።  አል-አሙዲ በኪሳራ ምክንያት የተዘጋውን የካራቱሪን እርሻ ጠቅልለው ሳይገዙት አይቀርም የሚል ወሬ በስፋት እየተሰራጨ ባለበት ጊዜ  መንግስት በድንገት ይህን እርምጃ መውሰዱ ከመለስ ሞት በሁዋላ የባለህብቱና-የመንግስት ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱን ጠቋሚ ነው ብለዋል-ዜናውን ያደረሱን ወገኖች።