መንግስት ለተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ ጥበቃ እንዲያደርግ ተጠየቀ

መስከረም ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-33ቱ ፔቲሽን ፈራሚ ፓርቲዎች ባወጡት መግለጫ ፣ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ትግላቸውን ለማስፋት በተጠናከረ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ መንግስት የህግ ጥበቃ ሊያደርግ ባለመቻሉ ከፍ ያለ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው ብለዋል።

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ በወላይታ፣ በአርባ ምንጭ፣ በፍቼና፣ በጎባ ከተሞች በተንቀሳቀሰባቸው ወቅቶች አባሎቻቸው መደብደባቸውን፣ መታሰራቸውን፣ የሥራ መሣሪያዎቻቸውን መነጠቃቸውን፣  ለመኝታ ገንዘብ የከፈሉበት ሆቴል በር እንዲዘጋባቸውና ደጅ እንዲያድሩ መደረጉን፣ የሚዘረዝረው መግለጫ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ ነሐሴ 19 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በአዲስ አበባ የመኢአድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ላዘጋጀነው ሕዝባዊ ስብሰባ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ የነበሩ ወጣቶች በልደታ፣ በነፋስ ስልክ ላፍቶና በአራዳ በጃን ሜዳ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን ጠቅሷል፡፡

ሠማያዊ ፓርቲ ነሐሴ 26 ቀን በመስቀል አደባባይ ከጠራው ሠልፍ ጋር በተያያዘ የመንግሥት ኃይሎች  በፓርቲውና በአባላቱ ላይ ሕገ ወጥ ድርጊት መፈፀማቸውንም መግለጫው አውስቷል።

ከመንግሥት ዋነኛ ኃላፊነቶች አንዱ የዜጎች መብቶች የሕግ ጥበቃ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ሆኖ ሳለ በተቃራኒው ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መንግሥታዊ  አካል ዜጎችንና በሕግ መሠረት የተደራጁ ፓርቲዎችን በሕገ ወጥ እርምጃ ለማንበረከክ ሲንቀሳቀስ መታየቱ  ለሐገር የከፋ ጉዳት እንዳለው የጠቀሰው የፓርቲዎቹ ስብስብ፣ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ከሚጥሱ ድርጊቶቹ እንዲታቀብና ለፓርቲዎች እንቅስቃሴ የሕግ ጥበቃ በማድረግ በተሻለ ሁኔታ በር እንዲከፍት፣ ሕዝቡ ለሕግ የበላይነት መከበር የሚያደርገውን ትግል በባለቤትነት አጠንክሮ እንዲቀጥል፣ የዴሞክራሲ ኃይሎችም ለሕገ መንግሥቱ ተግባራዊነት የተባበረ ትግላቸውን በይበልጥ እንዲገፉበት አሳስቦአል።

ፓርቲዎቹ ፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲ፣ ለሰብአዊ መብት መከበርና ለሕግ የበላይነት ከሚያደርገው ትግል ጎን እንዲቆሙ፣ የመገናኛ ብዙሃን በመንግሥት የሚፈፀሙ ሕገ መንግሥቱን የጣሱ እምርጃዎችን በተጨባጭ ለሕዝብ በማሳወቅ የሕዝብ ወገንተኛነታቸውን  እንዲያረጋግጡም ጠይቀዋል።